በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ አል-ሸባብን ማጥቃት ቀጥላለች


የአል-ሸባብ ታጣቂ
የአል-ሸባብ ታጣቂ

የሶማሊያ ጦር ሂራን ተብሎ በሚጠራው የሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ የአል-ሸባብ ተዋጊዎችን ኢላማ በማድረግ በርካቶችን መግደሉን የሃገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የቪኦኤው ሞሃመድ ዳህሴን ከዋጂድ ሶማሊያ እንደዘገበው፣ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር በሂራን፣ ቡሎ ቡርዴ ከተማ አቅራቢያ ዘምቶ ከሰላሳ በላይ የአል-ሸባብ ተዋጊዎችን ገድሏል ሲል የሃገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።

በዘመቻው አምስት ወታደሮቹ እንደተጎዱበት መንግስት አስታውቋል።

ሂራን በተባለችው የሃገሪቱ ክፍል በዚህ ወር ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመታየት ላይ ሲሆን፣ የሶማሊያ ጦር በርካታ ቦታዎችን ከአል-ሸባብ መንጠቁን ይናገራል።

አል-ሸባብ በሶማሊያ መንግስት በኩል በወጣው መግለጫ ላይ አስተያየት ባይሰጥም፣ ከአየር በተፈጸመ ጥቃት አንድ ባህላዊ መሪና ሌሎች ሲቪሎች መገደላቸውን ተናግሯል።

መረጃውን በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻልም።

በሌላ በኩል 10 የሚሆኑ የአል-ሸባብ ሰላዮችን የሃገሪቱ የመረጃና ደህንነት ተቋም ሞቃዲሹ ውስጥ መያዙን የሶማሊያ የሃገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አብዲካሚል ሞአሊም ሹክሪ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት የደህንነት ተቋሙ አል-ሸባብ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ሶስት ቤቶችንም በቁጥጥር ስር አውሏል።

አዲስ በፈጸመው ጥቃት ሃያ አንድ መንደሮችን ከአል-ሸባብ ማስለቀቁን የሶማሊያ መንግስት ሰሞኑን አስታውቋል። አንድ መቶ የሚሆኑ የአል-ሸባብ ተዋጊዎችን መግደሉንም ተናግሯል።

አል-ሸባብ ሞቃዲሹ በሚገኝ ሆቴል ላይ ጥቃት በማድረስ ከሃያ በላይ ሰዎችን ከገደለና ከመቶ ያላነሱትን ካቆሰለ በኋላ፣ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ማሃሙድ አስተዳደራቸው በአል-ሸባብ ላይ ሙሉ ጦርነት እንደሚያውጅ አስታውቀው ነበር።

XS
SM
MD
LG