በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፐሎሲ አዘርባጃን በአርሜኒያ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት አወገዙ


ናንሲ ፔሎሲ
ናንሲ ፔሎሲ

አርሜኒያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ም/ቤት አፈ ጉባኤ ናኒሲ ፐሎሲ በቅርቡ አርሜኒያ ላይ በአዘርባጃን የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘዋል።

ጥቃቱንም “ሕገ ወጥና አደገኛ” ሲሉ ጠርተውታል።

በአርሜኒያ መዲና የረቫን ላይ የተናገሩት ፐሎሲ፣ አሜሪካ የአርሜኒያን ሉአላዊነት እንደምትደግፍና ሃገሪቱ ራሷን ለመከላከል የሚያስፈልጋትን ነገር አሜሪካ ማወቅ ትሻለች ብለዋል።

ፐሎሲ አያይዘውም፣ ጥቃቱ የተጀመረው በአዘርባጃን ወገን መሆኑ መታወቅ አልበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

“አርሜኒያ ላይ በአዘርባጃን የተፈጸመው ጥቃት በዲሞክራሲና በፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች መካከል በመላው ዓለም የሚደረገው ትግል አካል ነው” ብለዋል ፐሎሲ።

የአዘርባጃን ሃይሎች ጀርሙክ የተባለውን የሽርሽር ከተማ በሰው አልባ አውሮፕላንና በሞርታር ደብድበዋል ሲል የአርሜኒያ መከላከያ ምኒስቴር ባለፈው ረቡዕ አስታውቆ ነበር።

የአዘርባጃን መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ የአርሜንያ ሃይሎች ይዞታዎቼን ደብድበውብኛል በማለት መልሶ ወነጅሏል።

አርሜኒያ 49 ወታደሮቿ እንደተገደሉባት ስታስታውቅ፣ አዘርባጃን ደግሞ 50 ሞተውብኛል ብላለች።

የሶቪየት ሶሻሊስት ሪፐብሊክ አካል የነበሩት ሁለቱ ሃገሮች ናጎርኖ ካራባክ በተባለው ክልል ይገባኛል ጥያቄ ለዓመታት ተዋግተዋል።

በእ.አ.አ. 1994 የአርሜኒያ ሃይሎች ናጎርኖ ካራባክን በቁጥጥር ሥር አውልውት የነበር ቢሆንም፣ ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገ የስድስት ቀናት ጦርነት አዘርባጃን ሰፊ አካባቢን ተቆጣጥራለች።

ሩሲያ አስታራቂ ሆና ጣልቃ በመግባት ሁለቱ ወገኖች የሰላም ስምምነት አድርገው እንደነበር ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG