በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ዩናይትድ ስቴትስ ጥሪ አቀረበች


የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ዩናይትድ ስቴትስ ጥሪ አቀረበች
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:21 0:00

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ወታደራዊ ግጭቶችን በአስቸኳይ በማቆም ወደሰላማዊ ሂደት እንዲመለሱ ዩናይትድ ስቴትስ በድጋሚ ጥሪ አቅርባለች። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ዩናይትድ ስቴትስን በይበልጥ እያሳሰባት ነው ብለዋል፡፡

በተቻለ ፍጥነት ውይይት ለማስጀመር የአፍሪካ ሕብረት የሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታደንቅና እንደምትደግፍም በድጋሚ ያረጋገጡት ቃል አቀባዩ ኤርትራ እና ሌሎችም ግጭቱን ከማባባስ እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡

ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ሁለት ሳምንት ለተጠጋ ጊዜ በቀጣናው የቆዩት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሀመር፣ አሁንም በቀጣናው እንደሚገኙም በትናንቱ መግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በትናንትናው ዕለት የአውሮፓ ሕብረት የውጭ አገልግሎት ቃል አቀባይ ያወጡትን መግለጫ “ስም አጥፊ” ያለው በቤልጂየም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ መግለጫ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል፡፡

በተያያዥ ዜና “በሰሜን ኢትዮጵያ እና በምስራቅ ዲሞክራሲያዊት ሪፖብሊክ ኮንጎ ለተፈጠረው ግጭት ኡሁሩ ኬንያታ የሰላም መልዕክተኛ ሆነው በአዲሱ ፕሬዚዳንት መሾማቸውን በደስታ እንደምትቀበል” ዩናይትድ ስቴትስ አስታውቃለች፡፡

በሌላ በኩል የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ መቀሌ ላይ በሰጡት መግለጫ፣ ድርጅታቸው በታሰበው የሠላም ድርድር ላይ ያለውን አቋም እና ሰሞኑን በግምባር ላይ አለ” ያሉትን ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

በተለያዩ ግምባሮች ጥቃት የከፈተው ህወሓት መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፣ በአራት ምዕራፍ የተከፈለ ዘመቻ እንደሚያደርግ እና የመጨረሻ ግብ ህወሓትን ትጥቅ ማስፈታት ስለመሆኑ አቶ ጌታቸው የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ ግን እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡

ድርድርን በሚመለከት ደግሞ ለአፍሪካ ሕብረት መራሽ ድርድር ዝግጁ መሆኑን ከህወሓት ቀድሞ ያሳወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ህወሓትም በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን ድርድር እንደሚቀበል ካሳወቀ በኋላ ቀጥተኛ ምላሽ ባይሰጥም፣ አሁንም በሕብረቱ ለሚመራው የሠላም ሂደት ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል፡፡

በሌላ በኩል ከድሮን ጥቃት ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ለቀረቡት ክሶችም የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ምላሽ ባይሰጥም ከዚህ ቀደም ለቀረበበት መሰል ክስ በሰጠው ምላሽ ግን አየር ኃይል ወታደራዊ ዒላማዎችን ብቻ ለይቶ እንደሚያጠቃ መግለጹ እና ህወሓት "ሆን ብሎ ሀሰተኛ እና አስከሬን የያዙ የሚመስሉ ከረጢቶችን ሰዎች በሚገኙበት ሥፍራ በማስቀመጥ" ቁጣ ለመቀስቀስ ይሞክራል በሚል መክሰሱ ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG