የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዩክሬን እየተካሄደ ሥላለው ጦርነት እንዲሁም በታይዋን ምክንያት የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ ለመነጋገር ሲልክ ሮድ በተሰኘችው በጥንታዊቷ የኡዝቤክስታን ከተማ ዛሬ ተገናኝተዋል።
ሁለቱ መሪዎች በተጨማሪም ሃይልነቷ እያደገ በመጣችው ቻይና እና በተፈጥሮ ሃብት በበለጸገችው ሩሲያ መካከል ስለሚደረግ ወዳጅነትና ትብብር ጉዳይ ላይ ይነጋገራሉ ሲል ሮይተርስ ከሥፍራው ዘግቧል።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ውጪ ሀገር የተጓዙት ሺ ጂንፒንግ ማዕከላዊ እሲያ የገቡት ትናንት ሲሆን፣ ይህም የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በሚቀጥለው ወር ጉባኤውን ከማካሄዱ ቀደም ብሎና፣ ሺ ጂንፒንግን ለሦስተኛ የአምስት ዓመት ሥልጣን ዘመን እንደሚመርጥ በሚጠበቅበት ሰዓት ነው። በዚህም ሺ ጂንፒንግ ከማኦ ዜዱንግ በኋላ ረጅምና ከፍተኛ ሥልጣንን የተቆጣጠሩ የቻይና መሪ ይሆናሉ።
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በጥንታዊቷ ከተማ ሳማርካንድ ዛሬ ከሰዓት በኋላ እንደሚገናኙ በሩሲያ የልዑካን በኩል የወጣው የጉዞ ፕሮግራም አመልክቷል።
ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች የጋራ በሆኑና እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ሲሉ የፑቲን የውጪ ፖሊሲ አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ ሞስኮ ላይ ማክሰኞ ዕለት ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
ሁለቱ መሪዎች ከዚህ በፊት የተገናኙት ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ ሲሆን፣ “ምንም ገደብ የሌለው” ትብብር ለማድረግ እንዲሁም ከምዕራቡ ዓለም በተቃራኒ ለሚደያደርጉት ትብብር ፊርማቸውን አኑረው ነበር።
ፑቲን ወደዛሬው ስብሰባ የሚገቡት ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ሃገራቸውን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ፍጥጫ ውስጥ ከዶለውና ሰባት ወራትን ካስቆጠረው የዩክሬኑ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ነው።
ፑቲን እስከአሁን ጦራቸው ከሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ሽንፈት ገጥሞት እየለቀቀ ስላለበት ሁኔት በአደባባይ አስተያየት ሰጥተው አያውቁም።
ሁለቱ መሪዎች በኡዝቤኪስታን የተገኙት የ”ሻንጋይ ትብብር ድርጅት ጉባኤ”ን ለመታደም ሲሆን፣ ይህም ስብስብ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ፓኪስታን እና አራት የማዕከላዊ እሲያ ሃገሮችን ያካተተ ነው። ኢራንም ስብስቡን ለመቀላቀል ዛሬ ፊርማዋን አኑራለች።
ፑቲን በኡዝቤኪስታን ቆይታቸው የህንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን ጨምሮ ከበርካታ የእሲያ ሃገራት መሪዎች ጋር ይገናኛሉ ተብሏል።