እስካሁን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 በተፈፀመው ጥቃት ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን፣ አሙሩ ወረዳ የተፈናቀሉ ዜጎች ተናግረዋል ።
በታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት ከአጋምሳ ከተማ እና አጎራባች ወረዳዎች የተፈናቀሉት እነዚህ ዜጎች በትምህርት ቤቶች እና በዕምነት ተቋማት ተጠልለው እንደሚገኙም ነው የገለፁት።
የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በበኩሉ የተፈናቀሉ ሰዎችን መረጃ ለመሰብሰብ የተዋቀረ ኮሚቴ ወደ አካባቢው ማምራቱን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጷጉሜ 1/2014 ባወጣው መግለጫ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጾ፣ በአፋጣኝ ዕርዳታ እንዲደረግላቸውም አሳስቦ ነበር።