ኢራን የኑክሌር ሃይልን ከሚቆጣጠረው ከተመድ ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ሃይል ተቋም ጋር እተባበራለሁ ስትል ዛሬ ሰኞ አስታውቃለች። ሆኖም፤ “ግዴታ ቢኖብኝም፣ መብትም ደግሞ አለኝ” ስትል አስታውቃለች።
የተመድ የኑክሌር ተቆጣጣሪው ባለስልጣን በኢራን ባልተገለጹ ቦታዎች ዩራኒየም ይገኝ እንደሆነ በመመርመር ላይ ነው።
የኢራን የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ለዜና ሠዎች እንዳሉት ኢራን ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ተቋምና ከቦርድ አመራሩ “ገንቢ የሆነ እርምጃ” ትጠብቃለች ብለዋል።
ቦርዱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የኑክሌር ጉዳዮችና የኢራን የኑክሌር ፕሮግራም አሳሳቢነት ላይ ዛሬ ስብሰባ ይጀምራል፡፤
ሰው ሰራሽ የሆነ የዩራኒዩም ቅንጣት በሶስት ያልተገለጹ ቦታዎች ላይ መገኘታቸውን በተመለከተ ኢራን ሃቁን እንድትናገር የዓለም አቀፉ አቲቶሚክ ተቋም ግፊት በማድረግ ላይ ተዘግቧል።
የኑክሌር መሳሪያ ታመርታለች በሚል ስጋት ሀገሪቱ ላይ የተጫነው ማዕቀብ እንዲላላ እ.አ.አ. በ2015 የተደረሰው የኑክሌር ስምምነት እንደገና እንዲያንሰራራ ለማስቻል፣ አሁን እየተደረገ ያለው ምርመራ እንዲያበቃ ኢራን ትሻለች።
“ኢራን የኑክሌር ድርድሩን ከምሯ እየወሰደች አይደለም” በሚል እንግሊዝ፣ ፈርንሳይ እና ጀርመን ባለፈው ቅዳሜ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
የኢራን የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ የሃገራቱን መግለጫ “ገንቢ ያልሆነ” ሲሉ አጣጥለውታል።
“የኑክሌር ስምምነቱ ለኢራን ያደላ ነው” በሚል የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በእ.አ.አ. 2018 የዩናይትድ ስቴትስን ከስምምነቱ አስወጥተው አዲስ ማዕቀብ ጥለዋል። ኢራን በአጸፋው ስምምነቱ ከጣለባት መጠን በላይ ዩራኒዩም ስታመርትና ሌሎች የኑክሌር ማምረቻ መሳሪያዎችን ስትገነባ ቆይታለች።