በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኬንያው ፍ/ቤት አወዛጋቢውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይወስናል


ፎቶ ፋይል፦ ራይላ ኦዲንጋ
ፎቶ ፋይል፦ ራይላ ኦዲንጋ

ኬንያዊያን የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ባላፈው ወር በተካሄደው ምርጫ አሸናፊ የሆኑትን የተመራጩ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶን ምርጫ ውጤት ያጸናል ወይስ ይሽራል የሚለውን ውሳኔ በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑ ተነገረ፡፡

በነሀሴው ምርጫ በዋናው ተፎካካሪያቸው ዊሊያም ሩቶ በትንሽ ልዩነት የተሸነፉት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ፣ የምርጫውን ውጤት አስመልክቶ ባቀረቡት አቤቱታ፣ የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

ሩቶ 7.1 ሚሊዮን ድምፅ ሲያገኙ፣ ኦዲንጋ 6.9 ሚሊዮን ድምፅ ማግኘታቸው ተመልክቷል፡፡ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ሩቶ የፍርድ ቤቱን ውሳኔን እንደሚያከብሩ ባለፈው እሁድ ተናግረዋል፡፡

የምርጫ ኮሚሽኑ ለሩቶ የሰጠውን ድምጽ አጨበርብሯል በማለት ኦዲንጋ ያቀረቡትን ክስ፣ ኮሚሽኑ ባላፈው ሳምንት በሰጠው ምላሽ ውድቅ አድርጎታል፡፡ የሩቶ አሸናፊነት ከተረጋገጠ፣ በሚቀጥለው ሳምንት ቃለ መሃላ በመፈጸም አምስተኛው የኬንያ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ፡፡

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ኦዲንጋን የሚደግፍም ከሆነ በ60 ቀናት ውስጥ በአገሪቱ ሌላ ምርጫ እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡

ፍርድቤቱ፣ የምርጫ አስፈጻሚው አካል፣ የምርጫውን ድምፅና ውጤት ያረጋገጠው፣ ህገ መንግስቱንና የምርጫ ህጉን ተክትሎ መሆን አለመሆኑን ተመልክቶ ይወስናል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ሪፖርተራችን ሞሀመድ ዩሱፍ ከናይሮቢ የላከው ዘገባ አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG