ባለፈው ሣምንት ባገረሸው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወደ ሙሉ ማጥቃት አለመግባቱን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።
ለሀገር ውስጥ የብዙኃን መገናኛ ጋዜጠኞች ዛሬ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደ’ኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ የመንግሥት ጦር “ከህወሓት በኩል ተከፍቷል” ያሉትን ጥቃት በመከላከል ላይ ብቻ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
መንግሥት “አሁንም ለሰላም ዝግጁ መሆኑን” ገልፀው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በህወሓት ላይ ጫና እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል “የትግራይ ክልል መንግሥት ፍላጎት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ነው” ሲሉ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለክልሉ የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ በትግራይ በኩል “ከፌዴራሉ መንግሥት በኩል ተከፍቶብናል” ያሉትን ጥቃት ከመከላከል ያለፈ ፍላጎት እንደሌላቸው አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ቀዳሚ ፍላጎታቸው የሰላም ጥያቄ መሆኑን ኢሰመኮ በምርመራ ማረጋገጡን የገለፁት የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ሁሉም የጦርነቱ ተሣታፊ ኃይሎች ለማኅበረሰቡ ፍላጎት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል መቀሌ ውስጥ ፈፅሟል በተባለው የአየር ጥቃት ስለደረሰው ጉዳት፤ እንዲሁም የህወሓት ተዋጊዎች ቆቦ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን በሚጠቁሙ ሪፖርቶች ላይ ኮሚሽኑ መረጃ እያሰባሰበ መሆኑንም ገልፀዋል።
/ዝርዝር ዘገባዎቹን ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ/