የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ “በትግራይ ክልል በሚገኝ “የመዋዕለ ህጻናት ላይ ተፈጽሟል” የተባለና ሁለት ህጻናትን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸው የተነገረበትን የአየር ጥቃት ማውገዙን የዩኒሴፍ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ካትሪን ረስል ዛሬ ቅዳሜ ያወጡትን የትዊት መልዕክት ጠቅሶ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) ዘግቧል።
የትግራይ የውጭ ጉዳዮች ቢሮ የተባለው አካል ባወጣው መግለጫ “መቀሌ ውስጥ ወታደራዊ ዒላማ በሌለበት የህፃናት መጫወቻ ሥፍራና መዋዕለ ህፃናት ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል” ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ሲቪሎች ላይ የተፈፀመ ድብደባ አለመኖሩን ገልፆ ክሱን ማስተባበሉንና ዒላማው ወታደራዊ ተቋማት መሆናቸውን መናገሩን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
የአየር ጥቃቱ ዘገባ ከመሰማቱ በፊት የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ መንግሥት ትግራይ ውስጥ የሚገኙ የተመረጡ የሕወሃት ወታደራዊ ይዞታዎችን እንደሚመታ ገልፆ ሲቪሎች ወታደራዊ ትጥቆችና ማሰልጠኛዎች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ መልዕክት አስተላልፎ እንደነበር ታውቋል።