ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የአውሮፓ ሕብረትና ኢጋድ የጦርነቱ መቀስቀስ እንዳሳሰባቸው ገልጸው ሁሉም አካላት በአስቸኳይ ግጭት እንዲያቆሙ ተማጽነዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥም ትናንት በሰጡት መግለጫ ሁኔታው እንዳስደነገጣቸው ገልጸው፣ የግጭቱ ተሳታፊዎች ግጭቱን በማቆም ለሰላም የሚደረገውን ጥረት እንዲቀጥሉ መጠየቃቸው ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ጦርነቱ ዳግም መቀስቀሱ በተገለጸበት በትናንትናው ዕለት፣ የትግራይ ባለሥልጣናት ለሰብዓዊ አገልግሎት የምጠቀመውን ነዳጅ ዘርፈውኛል ሲል የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ “የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ለእርዳታ ሥራው የሚጠቀመውን 570,000 ሊትር ነዳጅ የትግራይ ባለሥልጣናት ሰርቀዋል" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት፣ ዩናይትድ ስቴትስና የኢትዮጵያ መንግሥትም ድርጊቱን ያወገዙ ሲሆን፣ በህወሓት በኩል ግን እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡