በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደቡብ ሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ ተፈታች


ደቡብ ሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ ተፈታች
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:23 0:00

ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ጭማሪ በመቃወም ባለፈው ነኀሴ 1 ዋና ከተማዪቱ ጁባ ላይ የተካሄደውን ሰልፍ በመዘገብ ላይ እንዳለች በፖሊስ የተያዘችው ጋዜጠኛ ከስምንት ቀናት በኋላ ትናንት ተለቅቃለች።

የአሜሪካ ድምፅ የደቡብ ሱዳን ዘጋቢ ዲንግ ማጎት የታሰረችው ኮኞ-ኮኞ በሚባል የገበያ ሥፍራ ሲሆን መታወቂያ ሳትይዝ በመሥራት ተከሳለች።

በወቅቱ ሌሎች ስድስት ሰልፈኞችም ተይዘው ታስረዋል።

ጁባ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባለፈው ሣምንት ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኞች ያለማንም ጣልቃ ገብነትና የአደጋ ሥጋት ሥራቸውን የማከናወን መብት እንዳላቸው አስታውሶ ማጎት በአስቸኳይ እንድትለቀቅ ጠይቆ ነበር።

ማጎት ትናንት፤ ሰኞ በዋስ መለቀቋን ያስታወቁት የማጎት ጠበቃ ሴቨን ዋኒ ምርመራው ግን ሊቀጥል እንደሚችል ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። "ዋስትና አገኘች ማለት ጉዳዩ ውድቅ ሆኗል ማለት አይደለም። ምርመራው ሲጠናቀቅ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል።” ብለዋል።

በማጎት መፈታት ቤተሰቦቿ መደሰታቸውን የገለፀችው እህቷ አያን ማጎት "ከታሰረች ጀምሮ ለጉዳይዋ ጆሮ እንዲሰጡና በአስቸኳይ እንድትለቀቅ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሳይቀር ሁሉንም በር ስናንኳኳ ነበር" ብላለች።

ድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ድርጅት በየዓመቱ በሚያወጣው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ጠቋሚ ሠንጠረዥ ላይ ደቡብ ሱዳን ከ180 ሀገሮች 139ኛ ላይ የምትገኝ ሲሆን መረጃው አክሎ በሥራቸው ላይ ቅድመ-ምርመራ እንዲካሄድ የማይፈቅዱ የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኞች ለተደጋጋሚ ወከባ፣ ድንገተኛ እሥራት፣ የሥቃይ አያያዝና አንዳንዴም ለሞት እንደሚዳረጉ ያሳያል።

ማጎት መፈታቷን ያረጋገጡት የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኦዬት ፓትሪክ ቻርልስ በሰጡት ቃል አቃቤ ሕግ ጉዳዩን ለመመርመር ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል በሚል ሕገመንግሥቱ ከሚፈቅደው ጊዜ በላይ ታስራ መቆየቷን ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG