በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የታላቁ ኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ይፋ ሆነ


የታላቁ ኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ይፋ ሆነ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:33 0:00

የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቅ “የዲፕሎማሲውን በር በሰፊው የሚከፍት ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጉባ ተራራዎች ስር፣ መጋቢት 24/2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋዩ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ ሦስት መሪዎች የተፈራረቁበት እና አሁንም በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቁ ዛሬ ይፋ ተደርጓል፡፡

የግድቡ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ተጠናቆ ውሃው ከዛሬ ነሐሴ 6 ጀምሮ በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ መጀመሩን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሥፍራው አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የጋራ ሀብታቸው የሆነውን የዓባይን ወንዝ በትብብር ሊጠቀሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የግድቡ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት የተከናወነው፣ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና ሱዳን መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሶ በቀጠለበት ወቅት ነው፡፡

የግድቡ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ በአባይ ተፋሰስ የግርጌ ሃገሮች መካከል ትብብር እንዲኖር “የዲፕሎማሲውን በር በሰፊው የሚከፍት ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡ ግድቡ ኃይል ከማመንጨት ያለፈ ሀገራዊ ትርጉም እንዳለውም ያነሱት ፕሬዚዳንቷ፣ ይሄውም “ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ለዚህ መድረስ እንችላለን የሚል ነው" ብለዋል፡፡

3ኛውን ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት በመቃወም ግብጽ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ያስገባች ሲሆን “በግብፅ ጥቅም ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ጉልህ ጉዳት ኢትዮጵያ ሙሉ ኃላፊነት ትወስዳለች” ስትል በደብዳቤዋ ገልጻለች።

ሥምምነት የራቀው እና በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሲካሔድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድርም ከተቋረጠ ቆይቷል፡፡ ሀገራቱ ለመጨረሻ ጊዜ ለድርድር የተቀመጡት በሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም ነው፡፡

ኢትዮጵያ በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውኃ መጠን ላይ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም የሚፈልጉት ግብጽና ሱዳን እስካሁን ለተካሔዱት ድርድሮች አለመሳካት ግትር አቋም ይዛለች በማለት ኢትዮጵያን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በተቃራኒው ግትር አቋም የያዙት ግብጽና ሱዳን መሆናቸውን የምትገልጸው ኢትዮጵያ ለድርድሩ ውጤታማ አለመሆን ጣቷን የምትቀስረው በሁለቱ ሀገራት ላይ ነው፡፡

የግድቡን ሦስተኛ ዙር ሙሌት በማስመልከት ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ወቅታዊው የግድቡ ሁኔታ የሁለቱ ሀገራት ክስ ሐሰት መሆኑን እንደሚያጸባርቅ አመለክተዋል፡፡

በግድቡ ጉዳይ በሦስቱ ሀገራት መሃከል ያለው ልዩነት በንግግር እንዲፈታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመጠየቅ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ በካይሮ እና በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመርም ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ እና የኢትዮጵያ የልማት ፍላጎት በሰፊው መረዳታቸውን ገልጸው፣ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር በሚካሔደው የዲፕሎማሲ ጥረት፣ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥምምነት ላይ መድረስ ይቻላል ብለዋል።

በ2012 የክረምት ወቅት ላይ 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ ሙሊቱ የተጀመረው የኅዳሴው ግድብ፣ አሁን በሦስተኛው ዙር የያዘው የውኃ መጠን 22 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መድረሱ ተገልጿል፡፡ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፣ አጠቃላይ የማመንጨት አቅሙ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ነው።

ከኅዳሴ ግድቡ 13 የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች መካከል፣ 9ኛው ዩኒት ትናንት ሥራ የጀመረ ሲሆን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡ በሙሉ አቅሙ የማመንጨት ደረጃ ላይ እስኪደርስ አሁን ላይ እስከ 270 ሜጋ ዋት እንደሚያመነጭ ተገልጿል፡፡ ተመሳሳይ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው 10ኛው ዩኒት ባለፈው የካቲት 13/2014 ዓ.ም ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የግድቡ አጠቃላይ የግምባታ አፈጻጸም 83 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፣ በ 2 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የግድቡ ግምባታ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡

ከአፍሪካ ትልቁ የውኃ ኃይል ማመንጫ የሆው የኅዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ 145 ሜትር ከፍታ እና 1,780 ሜትር ርዝማኔ ይኖረዋል፡፡ ውሃው ከግድቡ ወደ ኋላ 240 ኪሎ ሜትር ድረስ እንደሚያርፍም ይጠበቃል፡፡

XS
SM
MD
LG