የኬንያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት ራሳቸው ከማወጅ እንዲቆጠቡ ተጠየቀ።
የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ቆጠራ አሁንም እየተካሄደ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስቀድመው ውጤቱን ከማወጅ እንዲቆጠቡ የኬንያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች አሳስበዋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ ቆጠራ ከጀመረ ሦስት ቀናት ያለፉ ሲሆን ገዢው ፓርቲ ያለማስረጃ ‘ቆጠራው ተጭበርብሯል’ በማለቱ ውጥረት እየተስተዋለ ነው።
የኬንያ መገናኛ ብዙኃንም ከየምርጫ ጣቢያው የሚያገኙንት ቁጥር እየደመሩ ያቀርቧቸው የነበሩ ዘገባዎችን “ለጥንቃቄ ሲሉ ከትናንት፤ ሃሙስ ጀምሮ ማቆማቸው” የተነገረ ሲሆን ሁለቱም ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ተቀራራቢ አኀዞችን እያስመዘገቡ መሆናቸውንም ሲናገሩ ቆይተዋል።
ከኮሚሽኑ የተሰማ ነገር ባይኖርም ለፕሬዝደንትነት የሚፎካካሩት ዕጩዎች የምርጫ ዘመቻ ኃላፊዎች አንደኛው ሌላውን በማጭበርበር እየወነጀለ የየራሳቸው ዕጩ ማሸነፉን አውጀዋል። እንዲያውም ለፈንጠዝያ እንዲዘጋጁ ሁሉ ጥሪ አድርገዋል።ራይላ ኦዲንጋና ዊልያም ሩቶ እራሳቸው ግን ስለ ምርጫው እስካሁን ምንም አልተናገሩም።
መገናኛ ብዙኃንና የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ሃገሪቱ ውስጥ ላንዣበበው አለመረጋጋት ተጠያቂ መሆናቸውን የኬንያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኃላፊ ዴቪስ ማሎምቤ ተናግረዋል።
“ጥንቃቄ ካልተደረገ በሁለቱም ጠርዙ ስለት ያለው ጦር ነው የሚሆነው፤ ያልተረጋገጡ የምርጫ ውጤቶች በዋናዎቹ የብዙኃን መገናኛዎችና በማኅበራዊ መድረኮች በፖለቲካ ተዋንያኑ በተከታታይ በመለቀቃቸው ኬንያውያን እየጨመረ ለመጣ ውጥረትና ፍርሃት ተጋልጠዋል” ብለዋል ኃላፊው።
“የራሳቸውን ውጤት የሚያውጁ ወገኖች ከምርጫ ጋር ተያዞ የሚመጣውን የሁከት ታሪክ ማስታወስ አለባቸው” ሲሉ የአንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ኃላፊው ዊኒ ማሳይ አሳስበዋል።
“ይህች ሃገር በፖለቲካ አለመስማማት ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ሁከትና ግጭቶችን አስተናግዳለች። ሁለቱም መሪ ተፎካካሪዎችና ደጋፊዎቻቸው ማሸነፋቸውን እየተነበዩ ውጥረቱን እያከረሩ ነው። እጅግ የበረታ የፓርቲ ወገንተኛነት ትዕግስትንና መረጋጋትን ያሳጣል” ብለዋል ማሳይ።
አንዳንድ የምርጫ ታዛቢዎች ደግሞ “ኮሚሽኑ በቆጠራው ላይ በጣም በማዝገሙ ለግምትና ለትንበያ በር ከፍቷል” እያሉ ነው።
በሌላ በኩል ሰሜን ኬንያ ውስጥ ሦስት የምርጫ ኃላፊዎች “የምርጫ ቁሳቁስ ከአግባብ ውጭ ይዘዋል” በሚል ተከስሰው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። በናይሮቢ የውጤት መቁጠሪያ ማዕከል ውስጥ “አጠራጣሪ ዕቃ ተገኝቷል” በሚል የኦዲንጋና የሩቶ የምርጫ ወኪሎች ተጋጭተዋል።
መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪ ያደረጉት የምርጫ ኮሚሽኑ ሃላፊ ዋፉላ ቼቡካቲ ባስተላለፉት ብርቱ ማሳሰቢያ “እባካችሁ የምርጫ ሥራተኞቹን አትጠይቋቸው። ምክንያቱም ሥራውን ያጓትታል። ያንን የምታደርጉ ከሆነ ቶሎ አንጨርስም። የፓርቲ ወኪሎች ሥራችሁን ሥሩ፤ አስትውሉ፣ ማስታወሻ ያዙ፤ ሥራው እንዲቀጥል አድርጉ” ብለዋል።
የመብቶች ተሟጋቹ ዊኒ ማሳይ ደግሞ “የፖለቲካ ፓርቲዎችና ወኪሎቻቸው ያልተረጋገጠ ውጤት በማወጅ ውጥረት እንዲባባስ ከማድረግ አሁኑኑ እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን” ብለዋል።
በየማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች የሚሠራጩ ወሬዎችን በመቆጣጠር ፓርቲዎቹና መሪዎቻቸው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና ህዝቡ ደግሞ ቆጠራውን በተመለከተ ያልተረጋገጠ ወሬ ከማናፈስ እንዲቆጠብ ማሳይ አሳስበዋል።
ከ46 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የሚደረገውን ቆጠራ የማጣራት ሂደት ለማገዝ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንደሚያሠማራ የምርጫ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ውጤቱን እስከ ፊታችን ማክሰኞ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።