በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቀድሞው ፕሬዚዳንት መኖሪያ በኤፍቢአይ ተበረበረ


 የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማር-አ-ላጎ ፍሎሪዳ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መግቢያ ነሐሴ/ 2/2014 ዓ.ም
የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማር-አ-ላጎ ፍሎሪዳ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መግቢያ ነሐሴ/ 2/2014 ዓ.ም

ማር-አ-ላጎ ፍሎሪዳ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በፌደራል የወንጀል ምርመራ ሠራተኞች መበርበሩን የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ አስታወቁ።

“ፍሎሪዳ ውስጥ ፓልም ቢች፤ ማር-አ-ላጎ የሚገኘው ቆንጆ ቤቴ አሁን ተከብቧል፤ ተወርሯል፤ በአንድ የኤፍቢአይ ወኪሎች ግዙፍ ቡድን ተይዟል” ብለዋል የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሰኞ ማምሻውን ባወጡት ረዥም መግለጫ። “ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር ስተባበር ከቆየሁ በኋላ ይህ በቤቴ ላይ የተደረገ ድንገተኛ ወረራ አስፈላጊም አግባብም አልነበረም” ሲሉ አክለዋል ትረምፕ።

በቀድሞው ፕሬዚዳንት ቤት ላይ ተካሄደ ያሉት ፍተሻ የሚገኝበት ሁኔታና ስፋት ለጊዜው በግልፅ ባይታወቅም ፕሬዚዳንቱ ጥር 13/2013 ዓ.ም. ዋይት ሃውስን ለቅቀው ሲወጡ ከቤተ መንግሥቱ ተወስደዋል በተባሉ የምሥጢር ሰነዶችን አሉባቸው በተባሉ እሽጎች ላይ የሃገሪቱ የፍትኅ መሥሪያ ቤት ምርመራ እያካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

ብርበራው ሲካሄድ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ የነበሩት ፕሬዚዳንት ትረምፕ ፍተሻው ለምን እንደተካሄደባቸው አልተናገሩም።

ትረምፕ ባወጡት መግለጫ ላይ የፍትኅ ሚኒስቴሩም ሆነ ፌደራሉ የምርመራ ቢሮ ያወጡት አስተያየት የለም።

ለፍትኅ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ዴና ኢቨርሰን ላቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያለውና ማንነቱ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ምንጭ ብርበራው የተካሄደው ሰኞ ቀን ላይ እንደነበረ ከመናገሩ ውጭ ዝርዝር ማብራሪያ አልወጣም።

ብሄራዊው መካነ መዘክርና አብያተ መዛግብት አስተዳደር ከጥቂት ወራት በፊት አውጥቶት በነበረ መረጃ ማር-አ-ላጎ ወደሚገኘው የቀድሞው ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት በተወሰዱት 15 እሽጎች ውስጥ ምሥጢራዊ ሰነዶችን ማግኘቱን ካሳወቀ በኋላ ጉዳዩን ወደ ፍትኅ ሚኒስቴር መርቶት እንደነበር ተዘግቧል።

እ.አ.አ. በ1978 ዓ.ም. የወጣው የፕሬዚዳንታዊ ሠነዶች ህግ “ጠቅላይ አዛዡ ሥራውን እንደለቀቀ ሁሉም ፕሬዚዳንታዊ መዛግብት የመንግሥቱ ንብረት ሆነው ወዲያው ለብሄራዊ አብያተ መዛግብት ጥበቃ እንደሚሰጡ” የሚደነግግ ሲሆን ሁሉም ፕሬዚዳንታዊ አብያተ መዘክርና አብያተ መፃህፍት የብሄራዊው አብያተ መዛግብት አካላት መሆናቸው ይታወቃል።

ፕሬዚዳንት ትረምፕ መንግሥቱን በምርመራ አያያዝ ምግባረ ብልሹነት ከስሰው ተካሄደ ያሉትን ከበባና ብርበራም “የፍትኅ ሥርዓቱን እንደመሣሪያ መጠቀም ነው” ብለዋል።

በመግለጫቸው “በአንድ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ላይ እንዲህ ዓይነት አድራጎት ተፈፅሞ አያውቅም” ያሉት ትረምፕ ፈታሾቹ ቤታቸው ውስጥ ያለ ካዝናቸውን መክፈታቸውን ጭምር ጠቁመዋል።

የትረምፕ ጠበቃ ኢቫን ኮርኮራን ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ላቀረበላቸው ጥያቄ መልስ አልሰጡም።

የፕሬዚዳንት ባይደን ዋይት ሃውስ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ቀድሞ የተነገራቸው ነገር ጨርሶ እንደሌለ መግለፃቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

XS
SM
MD
LG