በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሰላም ንግግር በኢትዮጵያ ሊጀመር እንደሚችል አሜሪካ ተስፋዋን ገለፀች


የሰላም ንግግር በኢትዮጵያ ሊጀመር እንደሚችል አሜሪካ ተስፋዋን ገለፀች
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:03 0:00

በመጪው ነሐሴ 3 በጎረቤት ኬንያ ከሚካሄደው ምርጫ በኋላ፣ በኢትዮጵያ የሰላም ንግግር ሊጀመር እንደሚችል ሲሉ አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን ጥንቃቄ የተሞላው ተስፋቸውን ገልፀዋል።

በጥቅምት 2013 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያ የፈነዳውን ዘግናኝ ጦርነት ለማስቆም ከህሓሃት ጋር መነጋገር የሚቻል መሆኑን ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ወር ተናግረው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እና መንግሥታቸው ከአማፂያኑ ጋር የሚደረገውን ድርድር በመሪነት መሸምገል ያለበት የአፍሪካ ኅብረት ነው የሚል አቋም ሲያንጸባርቁ የነበረ ሲሆን፣ ህወሃት በበኩሉ ደግሞ ያንን በመቃወም ንግግሩ በኬንያው መሪ ኡሁሩ ኬንያታ አደራዳሪነት ኬንያ መደረግ አለበት የሚል አቋም ይዟል።

በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መ/ቤት የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ሞሊፊ ድርድሩ በማን መሪነት ይካሄድ የሚለውን የሁለቱን ወገኖች ልዩነት ብዙም ቦታ ሳይሰጡት አልፈው፣ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አህመድ ከኡሁሩ ኬንያታ ጋር “አዎንታዊ ግንኙነት አላቸው፣ ጉዳዩ ኬንያ በነሐሴ ሶስት ምርጫ ስላለባት ነው” ብለዋል።

የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊዋ ትናንት ለአሜሪካ ሴኔት የውጪ ግንኙነት ኮሚቴ እንደተናገሩት፣ “አሁን ያለው ትኩረት በኬንያ በሚደረገው ምርጫው ላይ በሆነበት ሰዓት፣ የድርድሩን ቀነ ቀጠሮ መወሰን ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ የምንጠበቀው ጉዳይ ነው” ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድ አዲሱ የአሜሪካ ልዑክ ማይክ ሃመር በዚህ ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ንግግሩን ወደፊት ለማስቀጠል ስለሚቻልበትን እና ማድረግ የሚገባቸውን ጉዳይ በተመለክተ ከሁለቱም ወገኖች ጋር እንደሚነጋገሩ የአፍሪካ ጉዳይ ሃላፊዋ ሞሊ ፊ ተናግረዋል።

የትግራይ አማጺያኑ የፌዴራል መንግሥቱ ሰራዊት ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ አብይ ጦራቸውን ወደ ክልሉ ሲልኩ ጦርነቱ ፈንድቶ፣ በቁጥር የማይገመቱ ብዛት ያላቸው ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የዘር ማጽዳት አካሂዳለች ስትል አሜሪካ የረጅም ግዜ ወዳጇን ኢትዮጵያን ትከሳለች። ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ደግሞ ካለፈው ታኅሣሥ መጨረሻ ጀምሮ ኢትዮጵያን አግዋ ተብሉ ከሚጠራው የቀርጥ ነጻ ንግድ ተጠቃሚነት አግደዋል። ያ ውሳኔያቸው ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አንቀሳቅሶ ሃገራቸው ወደ አግዋ ተጠቃሚነት አንድትመለስ ዘመቻ በማድረግ ላይ ናቸው።

“ከአግዋ ተጠቃሚነት የመታገድ ውሳኔ የሚጎዳው በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉንም ሕዝቦች ነው፣ መንግስትን ለይቶ አይደለም የሚቀጣው። የትም ኖሩ የት ገበሬዎችን ይጎዳል፣ ነጋዴዎችንም እንዲሁ” ብለዋል ሴናተር ክሪስ ቫን ሆለን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊ-አሜሪካውያን ከሚኖሩበት ሜሪላንድ።

ሞሊ ፊ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ወደ አግዋ ተጠቃሚነት ትመለስ፣ አትመለስ የሚለውን ጉዳይ የባይደን አስተዳደር “በቅርብ እያጤነው” እንደሆነ ተናግረው፣ በማከልም አሁን አሜሪካ ለሚያሳስቧት ጉዳዮች መልስ ለማግኘት “የተሻለ ሁኔታ” ላይ እንገኛለን ብለዋል።

/ዘገባው የኤ.ኤፍ.ፒ ነው/

XS
SM
MD
LG