በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት ለማጠናቀቅ ዛሬ ኢትዮጵያ ገቡ


የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት ለማጠናቀቅ ዛሬ ኢትዮጵያ ገቡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:52 0:00

የላቭሮቭ የአፍሪካ ጉብኝት ሀገራቸው ዩክሬንን በመውረሯ ሳቢያ ከምዕራቡ ዓለም እየመጣባት ያለውን ውግዘት በመከላከል ላይ ያተኮረ ነው።

የምዕራቡ ዓለም ሀገራት፣ በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተከሰተው ከፍተኛ የምግብ እጥረት መባባስ ሩሲያን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ነገር ግን ኢትዮጵያ በበኩሏ ከትግራይ አማጺያን ጋር በምታደርገው ጦርነት ሳቢያ ከምዕራቡ ዓለም ግፊት የመጣባትና ከሩሲያም ጋር የረጅም ግዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያላት ሀገር ነች።

ሰርጌይ ላቭሮቭ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት የሚያገባድድዱት የኢትዮጵያን ባለስልጣናት አዲስ አበባ ላይ በማነጋገር ሲሆን፣ በዚህም ሀገራቸው በዩክሬን ላይ በምታካሂድው ጦርነት ምክንያት ሌሎች ሀገሮች በረሃብ እንዲጠቁ ሆኗል የሚለውን ክስ መከላከላሉን ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የውጪ ጉዳይ ምኒስትሩ በተጨማሪም ከትግራይ ሰራዊት ጋር በነበረው ግጭት የሰብዓዊ መብት በመጣስ ተወንጅላ ከምዕራቡ ሃገር ጋር የሻከረ ግንኙነት ውስጥ ከገባችው ኢትዮጵያ ጋር ሃገራቸው ግንኙነቷን የምታጠናክርበትንም መላ ይሻሉ ተብሏል።

ከሌሎች ሃያላን አገሮች እንፃር ሲታይ ሩሲያ በኢትዮጵያ ያላት ታይታ እጅግም ነው። እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ የዕርዳታ ዱካ የላትም። እንደ ቻይናም በመሰረተ ልማት ላይ ክፍተኛ ተሳትፎ የላትም።

ነገር ግን ሁለቱ ሃገሮች ጠንከር ያለ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው። በጥቅምት 2013 የትግራዩ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሩሲያ ኢትዮጵያ ላይ በተባበሩት መንግስታት ይደርስባት የነበረውን ጫና ስትከላከልላት ቆይታለች። ጉዳዮች በዝግ ስብሰባ እንዲታዮ እንዲሁም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ፣ በመብት ጥሰት ክስ በኢትዮጵያ ላይ ሊወጣባት የነበሩ የአቋም መግለጫዎችን አግዳለች።

በአዲስ ሳበባ ያሉ ሰዎች ከምዕራቡ ዓለም ይልቅ ለሩሲያ ያላቸውን ጥሩ አመለካከት መግለጻቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። የጠቅላይ ምኒስትር ዓብይ አህመድ መንግስት ለህወሃት ወገን ድጋፍ ከማድረጉ ሴራ ጀርባ ሆኖ ይመራል የሚል ሃሳብን ያዘለ ክስ በምዕራቡ ዓለም ላይ ያቀርባል።

ገለልተኛ ተመራማሪው ሞገስ ዘውዱ ተሾመ የሩሲያና የኢትዮጵያ ግንኙነት ጥልቅና ታሪካዊ ነው ይላሉ።

“በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅትም ቢሆን በወቅቱ ከነበረቸው ሶቪየት ህብረት ጋር በመወገን ኢትዮጵያ መልካም ግኑኝነት ነበራት። አሁን ኢትዮጵያ ገብታበት ካለው አጣብቂኝ አንጻርም ስናየው፣ ሩሲያ ባላት የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የውጪ ፖሊሲ የኢትዮጵያን አቋም ስትደግፍና በጸጥታው ምክርቤትም ከጎኗ ስትቆም ነው የምናየው” ብለዋል ተመራማሪው።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የጥቁር ባህር ተከፍቶ የስንዴ ምርት ለገበያ እንደሚቀርብ ማረጋገጫውን ከውጪ ጉዳይ ምኒስትር ላቭሮቭ ሊጠብቁ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል።

ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን በማሳደግ ራሷን ለመቻል ዕቅድ አላት። አሁን ባለው ሁኔታ ግን 40 በመቶ የሚሆነውን የእህል ፍልጎቷን የምትሸፍነው ከዩክሬንና ሩሲያ በምትገዛው ነው። ሰላሳ በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊም ከዓለም ገበያ ከሚሸመተው እህል ምፅዋት ጠባቂ ነው።

የትግራዩ ጦርነት ቀጥሎ በነበረበት ባለፈው ዓመት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር የፀጥታ ትብብር መፈራርሟ፣ ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን እርዳታ የገቱና፣ በእዲስ አበባ የሚገኙ የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማቶች ቅንድባቸውን በግርምት ከፍ እንዲያደርጉ አድርጓል።

በኦንታሪዮ ኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙት ፕሮፌሰር አወት ወልደሚካኤል እንደሚሉት ግን ሩሲያ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን የምዕራቡን ዓለም ተፅዕኖ መተካት አትችልም። በተለይም አሁን በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት መቀዝቀዙን ተከትሎ ጠቅላይ ምኒስትሩ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እየሞከሩ ያለበት ወቅት ነው።

“የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትርና የምዕራቡ ዓለም ግንኙነት ከስድስት ወራት ወይም ከአንድ ዓመት በፊት እንደነበረው መጥፎ አይመስለኝም። የምዕራቡ ዓለም ጠቅላይ ምኒስትሩንም ሆነ ፖሊሲያቸውን እንደ በጎ በመመልከት ላይ ነው። አዲስ አበባና የምዕራቡ ዓለም መዲናዎች ግንኙነታቸውን እያሻሻሉ ካለበት ሁኔታ አንጻር ስናየው፣ ጠቅላይ ምኒስትር ላቭሮቭ ነገሮችን ለመቀየር ብዙም ዕድል የላቸውም” ብለዋል ፕሮፌሰር አወት።

ባለፈው መጋቢት የሩሲያ ዩክሬንን መውረርን አስመልክቶ በተባበሩት መንግስታት በወጣው የአቋም መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ ድመጸ-ተአቅቦ አድርጋለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ላቭሮቭ ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዛቸው በፊት በዩጋንዳና ግብፅ ጉብኝት አድርገው ነበር።

የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዮዎሪ ሙሴቪኒ በመከላከያና ደህንነት ረገድ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት አንደሚሹ አስታውቀዋል።

ብግብፅ ጉብኝታቸው ደግሞ ሁለቱ ወገኖች የዩክሬን ቀውስ በሚቆምበት፣ ከሩሲያ እና ዩክሬን እህል ለገበያ ስለሚቀርብበት፣ ስለ ጋራ የንግድ ስምምነት፣ ቀጠናዊ ግጭቶች እንዲሁም ሩሲያ በግብጽ አየተከለች ባለው የኑክሌር ሃይል ማመንጫን በተመለከተ መክረዋል።

XS
SM
MD
LG