በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጋዜጠኛ ተመስገን በዋስትና የሚለቀቅ ከሆነ መከላከያ ሠራዊት “እርምጃ እወስድበታለሁ” ማለቱን ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት እንዳሳወቀ ጠበቃው ገለፁ


ጋዜጠኛ ተመስገን በዋስትና የሚለቀቅ ከሆነ መከላከያ ሠራዊት “እርምጃ እወስድበታለሁ” ማለቱን ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት እንዳሳወቀ የጋዜጠኛው ጠበቃ ገለፁ

- የ “አል ዐይን ኒውስ” ዘጋቢው አልዓዛር ተረፈ የሰባት ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶበታል

በፍትሕ መጽሔት ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ ዋስትና ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ዛሬ ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም ከሰዓት ተሰይሞ የነበረው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ይግባኝ ችሎት፣ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 21/2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረሽብርና የሕገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቅ ሰኔ 27/2014 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ያቀረበው ዐቃቤ ሕግ፣ የዋስትና መቃወሚያውን ከትናንት በስትያ ሰኞ ዕለት ማቀረቡን ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ ለቪኦኤ አብራርተዋል፡፡

በዐቃቤ ሕግ ቀርበዋል ከተባሉት የዋስትና መቃወሚያዎች መካከል “የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ እርምጃ የመውሰድ ፍላጎት እንዳለው የሚገልጽ ይገኝበታል፡፡

“ጋዜጠኛ ተመስገን በዋስትና ተፈትቶ መጻፉን የማያቆም ከሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ እንወስዳለን ያለን ስለሆነ፣ ፍርድ ቤት ዋስትናውን ሊጠብቅለት አይገባም” በማለት ዐቃቤ ሕግ መከራከሪያ ማቅረቡን ነው አቶ ሄኖክ ተናግረዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ እወስዳለሁ ስላለው እርምጃ ግን በዝርዝር የተባለ ነገር እንደሌለም አመልክተዋል፡፡

“ከመከላከያ ሠራዊት እርምጃ ጋር በተያያዘ በዐቃቤ ሕግ የቀረበው የዋስትና መቃወምያ አዲስ መከራከሪያ ነው” ያሉት አቶ ሄኖክ፣ ሆኖም የመልስ መልስ ለተሰጠበት ጉዳይ መልስ ለመስጠት ሕጉ ስለማይፈቅድ በተመስገን በኩል የተሰጠ ምላሽ እንደሌለ አመልክተዋል፡፡

የተመስገንን መዝገብ እያየ መሆኑን ያስታወቀው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የወንጀል ይግባኝ ችሎት፣ መዝገቡን አይቶ እንዳልጨረሰ በመጠቆም ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 21/2014 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

ከግንቦት 18/2014 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዐቃቤ ሕግ የቀረቡበት ሦስት የወንጀል ክሶች፣ “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለሕዝብ መግለፅ”፣”የሐሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ ማሰራጨት” እና “መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር መፈፀም” የሚሉ ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ “አል ዐይን ኒውስ” የተባለ ዲጂታል ሚዲያ የአማርኛ ቋንቋ ጋዜጠኛ የሆነው አልዓዛር ተረፈ ትናንት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡

ሰኞ ዕለት በነበረው ክርክር ፖሊስ በጋዜጠኛ አልዓዛር ላይ የጀመረውን የምርመራ መዝገብ ባለመቅረቡ ምክንያት በዋስትናው ጉዳይ ላይ ውሳኔ መስጠት አለመቻሉን ፍርድ ቤቱ ገልጾ ነበር፡፡ በመሆኑም መዝገቡን ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ለትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀጠሮ ይዞ የነበረው ፍርድ ቤቱ፣ መዝገቡን ተመልክቶ ቀጥታ ትዕዛዝ መስጠቱን የአልዓዛር ጠበቃ አቶ መሰረት የኔሁን ተናግረዋል፡፡

ጠበቃው ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ሲያስረዱ፣ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ “አልዓዛር ብሔርን ከብሔር፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት የሚያጋጩ የቅስቀሳ መልዕክት ያላቸውን ጹሑፎች የጻፈው በሚሠራበት የአል ዐይን ሚዲያ ላይ ነው” የሚል ሲሆን ፣ “አል ዐይን ኒውስ” ፈቃድ ያለው ስለመሆን አለመሆኑ አጣርቶ እንዲቀርብ ለፖሊስ የሰባት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶታል።

በመሆኑም ፖሊስ ጉዳዩን አጣርቶ ሰኞ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም ማስረጃ ይዞ እንዲቀርብ ታዟል፡፡

ሐምሌ 7/ 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ላምበረት አካባቢ ከሚገኝ ካፌ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች የተያዘው አልዓዛር ተረፈ፣ ከጋዜጠኝነት ሥራው ጋር በተያያዘ በወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ሲውል የአሁኑ የመጀመሪያው ነው፡፡

አልአዛር በፖሊስ በተያዘ ማግስት ዓርብ ሐምሌ 8 በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ ችሎት ቀርቦ በ5 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቅ ተወስኖለት ነበር፡፡ ፖሊስ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝም ውድቅ ተደርጎበት የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲጸና ታዞ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ጋዜጠኛው ሳይፈታ ቆይቶ ሰኞ ሐምሌ 11 ነው የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርቧል፡፡

XS
SM
MD
LG