በሶማሊያ የጆሃር ከተማን ያናወጠ የመኪና ላይ አጥፍቶ ጠፊ ጥቃት በትንሹ 3ሰዎች እንደ ገደለ እና 7 ሰዎችን እንዳቆሰለ ተሰማ። ከፍተኛ የክልል ባለስልጣናት ከተጎዱት መካከል እንደሚገኙበት ተነግሯል።ሄርሻበሌ ተብሎ በሚጠራው ግዛት ለደረሰው ጥቃት አልሸባብ የተባለው ታጣቂ ቡድን ኃላፊነቱን ወስዷል።
የሂርሻበሌ ግዛት የሰብዓዊ ድጋፍ እና አደጋ ጊዜ አስተዳደር ሚኒስትር የሆኑት አብዲፈታህ ቆርካጋብ ለአሜሪካ ድምጽ እንደተናገሩት ፣ ጥቃቱ ያነጣጠረው የግዛቲቱ ህግ አውጪዎች፣ ሚኒስትሮች እንዲሁም ሌሎች ባለስልጣናት በሚያዘወትሩት ኑር ደብ የተሰኘ ሆቴል ላይ ነው። የግዛቲቱ የጤና ሚኒስትርን ጨምሮ የተጎዱ ሰዎች በአካባቢው ወደ ሚገኝ ሆስፒታል ለህክምና መላካቸውን ተናግረዋል ።
የሶማሊያ ፓርላማ አባል የሆኑት የግዛቲቱ እንደራሴ ሞሃመድ ኢብራሂም ከጥቃቱ በኃላ በጆሃር ከተማ የተፈጠረው ሁሉ በእጅጉ አስደንጋጭ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሰላማዊ ሰዎች መጠቀሚያ በሆነ የግል ሆቴል ላይ ጥቃት መክፈት የፈሪዎች የጭካኔ ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል። የተሰማቸውን ሀዘንም ለጥቃቱ ሰላባ ቤተሰቦች ገልጸዋል ።
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲ ባሬ ጥቃቱን አውግዘዋል።ጆሃር ከሶማሊያ ዋና ከተማ በስተ ሰሜን 90 ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት