በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሠላም ኮሚቴው ሥራ ጀመረ


ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ
ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ

ከህወሓት ጋር ሊደረግ ለሚችል ድርድር የተቋቋመው "የሠላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ" ዛሬ የመጀመሪያ ስብሰባውን ማካሄዱን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪና የኮሚቴው አባል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደጠቆሙት ኮሚቴው ሥራ የጀመረው በንዑሳን ኮሚቴዎች በመደራጀትና ኃላፊነት በመከፋፈል ነው።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለው ግጭት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ መወሰኑን ያስታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ዓላማ የተሠየመውን የተደራዳሪ ቡድን ይፋ ያደረገው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነው።

ለሠላም ዝግጁ መሆኑን የገለፀው ህወሓት በበኩሉ የልዑካን ቡድን የሚልከው ግን በኬኒያ መንግሥት ሰብሳቢነት እና አስተናጋጅነት ለሚካሄድ ውይይት መሆኑን አመልክቷል። በአፍሪካ ሕብረትም ሆነ የአህጉራዊው ተቋም ልዩ መልዕክተኛ በሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ላይ እምነት እንደሌለውም ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የሠላም ውይይቱ በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት መካሄድ እንዳለበት መወሰኑን በተደጋጋሚ አስታውቋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስለ ዛሬው የሠላም ኮሚቴ ስብሰባ ያሰፈሩት ጽሁፍም ይሄንኑ አቋም አንፀባርቋል።

ኮሚቴው "በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ለሚካሄደው ንግግር የራሱን የአሠራር እና ስነምግባር አካሄድ ተወያይቶ ወስኗል" በማለት ነው የገለፁት።

"የሠላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ" ሲሉ የገለፁትንና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራውን ቡድን የመጀመሪያ ስብሰባ ይዘትና ውጤት ግን በስፋት አላብራሩም።

XS
SM
MD
LG