በረቂቅ ሰነዱ ላይ ድሬዳዋ የከተማ አስተዳደር ሳይሆን “ድሬዳዋ አስተዳደር” ተብላ እንድትጠራ የታሰበ ሲሆን መሪዋም “ከንቲባ” ሳይሆን “ርዕሰ መስተዳድር” ይባላል ተብሏል። በገቢ አሰባሰብ በኩልም የፌዴራል መንግሥቱ ከድሬዳዋ ከሚሰበስበው ገቢ የተወሰነው ለድሬዳዋ ገቢ እንዲሆን ታስቧል።
በአስተዳደሩ ከማዕከልና ቀበሌ ባሻገር የወረዳ መዋቅርም የሚኖር ሲሆን የፖሊስ ኮሚሽን እና ምርጫ 97ትን ተከትሎ ወደ ፌዴራል መንግሥቱ ተዛውረው የነበሩ የተዛወሩ ተቋማት ተጠሪነታቸው ለድሬዳዋ አስተዳደር እንዲሆን የቻርተሩ ረቂቅ ይጠይቃል።
በሌላ በኩል አብላጫውን የአስተዳደር ምክር ቤት ወንበር ከከተማው ነዋሪ በግማሽ ያነሰ ቁጥር ላላቸው የገጠር ቀበሌዎች የደለደለው ነባሩ የምክር ቤት አባላት ቁጥርና አወካከልን በተመለከተ በአዲሱ ረቂቅ ላይ በግልጽ የተባለ ነገር የለም።