የሀገራቸውን ፕሬዚደንት ጎታባያና ራጃፓክሳ መኖሪያ ቤት በመቆጣጠር ፣ በሀገሪቱ የባህር ኃይል ድጋፍ እንዲሸሹ ብሎም ከስልጣን እንዲለቁ ያደረጉት የሲሪ ላንካ ተቃዋሚ ሰልፈⶉች አሁንም ከፕሬዚደንቱ መኖሪያ ቤት ለመልቀቅ አልፈቀዱም ።
የተማሪዎች እንቅስቃሴ ፕሬዚደንት የሆነው ፣ ላሂሩ ዊራስካራ “ትግላችን ገና አላበቃም!” ሲል ለዘጋቢዎች ተናግሯል፣ በአሁኑ ሰዓት በደሴቲቱ ደቡባዊ የባህር ወሰን ላይ በሚገኝ መርከብ ውስጥ የተጠለሉት ራጃፓክሳ ፣ ከስልጣን መልቀቃቸውን ረቡዕ ዕለት ካስታወቁ በኃላ፣ ከስልጣን የመልቀቃቸው ነገር እርግጥ እስኪሆን ድረስ ፣ ትግሉ እንደማይቆም ዊራስካራ አክሏል ።
የቅዳሜው ዕለት ክስተት ፣ በደቡባዊ እስያዊት ደሴት የደረሰው ያልተጠበቀ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና የራጃፓክሳ ቡድን የአመራር ድክመት እና ሙስና የቀሰቀሰው ለወራት የዘለቀው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጣሪያ ተደርጎ ተቆጥሯል።
በመቶሺ የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ራጃፓክሳ ፣ በአንድ ወቅት በተነጻጻሪነት ሀብታም የነበረችውን ሀገር በማሽመድመድ በህዝቧ ላይ መከራን ላመጣው፣ የመድሃኒት ፣ ምግብ እና ነዳጅ እጥረት ኃላፊነት እንዲወስዱ ነበር ለተቃውሞ የወጡት።
በቅኝ ግዛት ዘመን የተገነባውን፣ የፕሬዚደንቱን ቤተመንግስት ሰብረው የገቡት ተቃዋሚዎች፣ በቅንጡ ክፍሎች ውስጥ ተሰይመዋል፣ በመዋኛ ገንዳው ውስጥ ተምነሽንሸዋል፣ የፕሬዚደንቱን አልባሳት ፈትሸዋል ።
ይሄ ከመሆኑ አስቀድሞ፣ ራጃፓክሳ እንዲያመልጡ ለመርዳት ወታደሮች ወደ ሰማይ የተኮሱ ሲሆን፣ ፕሬዚደንቱ የባህር ኃይል ጀልባ እንዲሳፈሩ ተደርገው ለደህንነታቸው ወደ ሀገሪቱ ደቡባዊ ውሃማ ቀጠና ተወስደዋል ።
በዛሬው ዕለት ለሁሉም ዜጋ ክፍት በነበረው የፕሬዚደንቱ መኖሪያ ውስጥ ህጻናት እና ወላጆቻቸው በስፍራው የሚገኘውን ፒያኑ ሲቆረቁሩ፣ ቅንጡ የጥበብ ስራዎችን ሲያደንቁ፣ በፕሬዚደንቱ ወንበር ላይ በየተራ ሲቀመጡ ውለዋል። ዘገባው የኤ ኤፍፒ ነው።