የጃፓኑ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ አስክሬን በሞተረኞች ታጅቦ ግድያው ከተፈጸመበት ከናራ ከተማ ወደ ቶክዮ ተመልሷል። በሺንዞ መኖሪያ ቤት አካባቢም ለቀስተኞች ተሰባስበው ታይተዋል። የሺንዞን ግድያ የሃገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት መዋቅር ‘በዴሞክራሲ ላይ የተደረገ ጥቃት’ ሲል ገልጾታል።
ፖሊስ የ41 ዓመቱን ጥቃት አድራሽ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስል ሊያውለው ችሏል። የአካቢው ፖሊስም የነበረው የጸጥታ ሁኔታ የላላ እንደነበር አምኗል። የናራ ከተማ የፖሊስ ሃላፊ ቶማይኪ ኦኒዙካ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የተፈጠረውን ሁኔታ ካየን በኋላ የደህንነት ክፍተት አልነበረም ልንል አንችልም” ብለዋል።
ሃላፊው የተፈጠረውን ሁኔታ መርመረው አስፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ በማረጋገጥ “ከፍተኛ የሆነ ሃላፊነት ይሰማኛል” ሲሉ አስታውቀዋል።
የጃፓን ከፍተኛ ምክር ቤት ምርጫም በተያዘለት ቀጠሮ መሰረት በነገው ዕለት ይካሄዳል። የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ አርብ ዕለት ከተኩሱ በኋላ በአስቸኳይ ወደ ቶኪዮ ተመልሰው የክልል ሃላፊዎችን ካዋዩ በኋላም በድጋሚ ለምረጡኝ ቅስቀሳ ወጥተዋል።
ግድያውን ተከትሎም እጅግ ከወንጀል ነጻ በሆነችው ጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሺዳ የምረጡኝ ዘመቻ ንግግር ሊያደርጉ እየተሰናዱ ባሉባት የጃፓኗ ፉጂዮሺዳ ከፍተኛ የብረት መመርመሪያ መሳሪያዎች ተተክለዋል።
በተመሳሳይ ከቶኪዮ 450 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በተገደሉባት ናራ ከተማም ብዙዎች የሺንዞ አቤ ፎቶ በተቀመጠበት ስፍራ ላይ የመታሰቢያ አበቦችን እያስቀመጡ ይገኛሉ።
የ ሺንዞ አቤ ባለቤት የሆኑት የ50 አመቷ እመቤት ናቱሳሚ ኒዋ ከ10 ዓመት ልጃቸው ጋር ግድያው በተፈጸመበት አቅራቢያ የመታሰቢያ አበባ ካስቀመጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር “በናራ በተፈጠረው ነገር ደንግጫለሁ” ብለዋል።
የሺኖዞ አቤ የቀብር ስነስርዓት በመጪው ማክሰኞ የሚደረግ ይሆናል።