በኦሮሚያ ክልል የወለጋ ዞኖች በንጹኃን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሚለውና መንግሥት ሸኔ ብሎ በሚጠራው ቡድን መፈጸሙን ኢሰመኮ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይህን ያስታወቀው፣ ከሰኔ 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም የነበረውን ዓመታዊ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ዛሬ ሐምሌ 1/2014 ዓ.ም ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ታጣቂ ቡድን መሰል ውንጀላዎችን በተደጋጋሚ ማስተባበሉ ይታወቃል፡፡
ይህን በመግለጽ ከቪኦኤ ጥያቄ የቀረበላቸው የኢሰመኮዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል የሚባል አካል፣ የሚቀርብበትን ውንጀላ ማስተባበሉ የተለመደ ነው ብለዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና ከመንግሥት ውጭ በሆኑ የታጠቁ ኃይሎች “እጅግ አስከፊ የሆኑ” ያሏቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት አመልክተዋል፡፡
ሪፖርቱ፤ ኮሚሽኑ በዓመቱ ባደረገው ክትትልና ምርመራ፣ ባከናወናቸው መለስተኛ ጥናቶች፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሔደውን ጦርነት ተከትሎ ባካሔዳቸው ምርመራዎች እና በሌሎች መረጃዎች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡