የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሚያስፈልገው በጀት ውስጥ የ426 ሚሊዮን ዶላር ጉድለት ያጋጠመው በመሆኑ በደቡብ ሱዳን ለ1.7 ሚሊዮን የሚሰጠውን የምግብ እርዳታ ለማቆም መገደዱን አስታውቋል፡፡
ግጭት፣ ሦስት ዓመታት ያከታተለው የጎርፍ አደጋ፣ የአገር ውስጥ ድርቅ ፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ የናረው የምግብ ዋጋ፣ እና የዩክሬን ጦርነት ደቡብ ሱዳንን አንበርክኳታል፡፡
በደቡብ ሱዳን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተጠባባቂ ዳይሬክተር አዴንካ ባዴጆ፣ አገሪቱ ነጻነቷን ካገኘችበት የ2011 ዓ.ም የአውሮፓውያን አቆጣጠር ጀምሮ፣ ከፍተኛ ለሆነው የምግብ ደህንነት ችግር መጋለጧን ይናገራሉ። ከአገሪቱ መዲና ጁባ በሰጡት መግለጫ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በዚህ ዓመት 6.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ለመርዳት እቅድ ነበረው። ይሁን እንጂ የጥሬ ገንዘብ እጥረት የገጠመው በመሆኑ ምግብን እጅግ ከተራቡት ሰዎች ለማራቅ መገደዱን ገልፀዋል።
“እነዚህ የድጋፍ ማቋረጦች የሚከሰቱት ቤተሰቦች ያላቸውን የምግብ ክምችት በሙሉ ባሟጠጡበት፣ ችግሩ እየበረታ ሄዶ ረሀቡ እየጠና በመጣበት ጊዜ ነው።” ያሉት አዴንካ ባዴጆ ፤ “እኛ ያለንን አቅም ሁሉ ተጠቅመን ትኩረታችን ያደረግነው በከፍተኛው ረሀብ አፋፍ ላይ ያሉትን እና ለረሀብ የተጋለጡትን የተወሰኑ ሰዎች ከረሀብ አደጋው በመካለከሉ ላይ ነው።” ብለዋል።
ባዴጆ የገንዘብ ድጋፉ ያለበት ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ተቋም ተጠቃሚዎች የሚያገኙትን የምግብ ድርሻ በግማሽ እንዲቀንስ ያስገደደ በመሆኑ እጅግ ወሳኝ ነው ይላሉ። እነዚህ ድጋፎች የተቋረጡት የምግብ ክምችቶቹ እጅግ አንሰተኛ በሆኑበት ጊዜ መሆኑን ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡ የረሀቡ አደጋ እጅግ በሚጠናበት የሐምሌው ወር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፍተኛ ረሀብ እንደሚጋለጡም ተናግረዋል፡፡
ባዴጆ ከዚህም ጋር ተያይዞ ብዙ ሰዎች ረሀቡን ለመቋቋም እና በሕይወት ለመቆየት ሲሉ ተቃራኒ ውጤት የሚሰጡ ያልተገቡ ነገሮችን እንዲያደርጉ ሊገደዱ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
“በምዕራብ ባኽር ኤል ጋዛል ካሉት የቡድን አባላት ጋር ከፍተኛ የተመጣጠነ የምግብ ጉድለት መኖሩን ተመልክተናል፣ የአካባቢው ማኅብረሰብ አባላት ራሳቸውን በሕይወት ለማቆየት ሲሉ ለሚሸጡት ከሰል በተደጋጋሚ ዛፎችን እየጨፈጨፉ መሆኑን ዘገባዎች ደርሰውናል፡፡” ያሉት ባዴጆ “ባላፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በየጎዳናው ላይ የሚለምኑ ሕጻናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አይተናል፡፡” ብለዋል።
የለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍና ከወዲሁ አስቀድሞ የሚወሰድ ሰብዓዊ እምርጃ አደገኛውን ቀውስና የሰዎችን ሕይወት ሊያድን ይችላል ሲሉ ዓለም አቀፍ የምግብ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡