“የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ ሰብዓዊ መብቶች ልዩ መርማሪ በዚያች አገር ያለው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እያሽቆለቆለ ነው” ያለበትን ዘገባ አወጣ።
“ለወታደራዊ ግዳጅ መመልመል፣ የዘፈቀደ እስር፣ የገቡበት ሳይታወቅ ደብዛ ጠፍቶ መቅረት እና ለሥቃይ መዳረግ ይገኙበታል” የሚለው ልዩ ሪፖርት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንዲቀርብ ተደርጓል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የኤርትራ ጉዳይ ልዩ መርማሪ መሃመድ አብደልሰላም ባቢከር “ኤርትራ በጎረቤት ኢትዮጵያው ወታደራዊ ግጭት መሳተፏ የኤርትራ መንግሥት በሚያራምደው የጊዜ ገደብ የሌለው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ሥርዓት ዙሪያ የተለየ ትኩረት ስቧል” ብለዋል።
“በኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ እጅግ አስከፊ ነው” ያሉት ባቢከር አክለውም “በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎቱ ላለመሳተፍ የሞከሩ ሰዎች ሰብዓዊነት በጎደለው እና ሰብዓዊ ክብርን በሚያዋርድ መንገድ ላልተወሰነ ጊዜ ይታሰራሉ።” ብለዋል።
“ባለሥልጣናቱ በተጨማሪም በብሔራዊ ውትድርናው ላለመሳተፍ የወሰኑ እና የጠፉ ሰዎችን በተዘዋዋሪ ወይም በውክልና ይቀጣሉ።” ካሉ በኋላ ይህንን በምሳሌ ሲያስረዱ “የጠፋውን ግለሰብ ወላጅ ወይም የትዳር ጓደኛ በማሰር እጅ እንዲሰጥ ስለመደረጋቸው እና በግዳጅ የተመለመሉ ወታደሮች ከትግራይ ወይም ከኤርትራ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ጠፍተው ለማምለጥ ሲሞክሩ ስለመገደላቸው የሚያወሳ ሪፖርትም ደርሶኛል።” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ጥቅምት 25/2013 ዓ.ም በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ላይ ወታደራዊ ዘመቻውን ከፈተ” ያለው ሪፖርት አክሎም “ከዚያን ጊዜም አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ወታደሮች በወታደራዊው በግዳጅ በግጭቱ እንዲሳተፉ ተገደዋል።” ብሏል።
“ዕድሜያቸው 14 ዓመት የሚሆን ታዳጊ ልጆች ጭምር ተመልምለው ተወስደዋል። በኢትዮጵያ በስደተኛ መጠለያ ካምፖች ውስጥ የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ታግተው ተወስደው እንዲዋጉ ተደርገዋል” ሲሉ ባቢከር ተናግረዋል።
ልዩ መርማሪው አያይዘውም “በኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ አሁንም በሺሆች የሚቆጠሩ አገር ጥለው ጥገኝነት ፍለጋ እንዲሰደዱ መግፋቱን ቀጥሏል” ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት አያያዝ መስፈርቶችን በጣሰ መንገድ ደብዛቸው የጠፉ ወይም በድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ በዘፈቀደ የታሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው የገለፁት አብዱልሰላም ባቢከር፤ “‘ቪላ’ እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ ተይዘው ስላሉ እና የስቃይ ምግባር ስለተፈጸምባቸው ሰዎች ከተጎጂዎች ከራሳቸው እና ከእማኞች የሚሰጡትን የምስክርነት ቃል አሁንም እሰማለሁ። እነኚህ በግልጽ ሊታወቁ የማይችሉ ሚስጥራዊ የእስር ቦታዎች ናቸው።” ብለዋል።
አምባሳደር ተስፋሚካኤል ገራህቱ በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመንግሥታቸው ተጠሪ ናቸው።
“ተመርጠው ከተጠየቁ እና ኃላፊነት ከጎደላቸው ምንጮች በተገኙ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ነው” ባሉት ሪፖርት ላይ “አጸያፊ” ላሉት ውንጀላ ምላሽ እንደማይሰጡ ተናግረዋል። ኤርትራ ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብአዊ መብት ቀውስ ያለመኖሩን ገልጸው፤ “በአገራቸው ላይ የሚፈጸም ትንኮሳ እና ማዕቀብ መቆም አለበት” ብለዋል።
ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና እንድታገለግል እአአ በጥቅምት 2021 በድጋሚ ተመርጣለች። ይሁንና እንደ ልዩ መርማሪው አስተያየትት ኤርትራ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ማራመድ እና ለዜጎች መብት የሚሰጠውን ከለላ ማረጋገጥ ያለመቻሏ የምክር ቤቱን ታማኝነት እና ተሰሚነት አደጋ ላይ ይጥለዋል።” ሲሉ ተችተዋል።