በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ የሚገኙ ሕጻናት ከርሃብና ሞት ጋር ተፋጠዋል


ፎቶ ፋይል - ሶማሊያ ውስጥ ዶሎ ጌዶ በተባለ አካባቢ ዶሎ ሆስፒታል ውስጥ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ እናቶች ልጆቻቸው በእግራቸው ላይ ታቅፈው የተመጣጠነ ምግብ በመጠባበቅ ላይ እያሉ። /እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ግንቦት 24/2022 ዓ.ም/
ፎቶ ፋይል - ሶማሊያ ውስጥ ዶሎ ጌዶ በተባለ አካባቢ ዶሎ ሆስፒታል ውስጥ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ እናቶች ልጆቻቸው በእግራቸው ላይ ታቅፈው የተመጣጠነ ምግብ በመጠባበቅ ላይ እያሉ። /እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ግንቦት 24/2022 ዓ.ም/

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የተራቡ እና በተመጣጠነ የምግብ እጦት የተቸገሩ ሕጻናትን ሕይወት ለመታደግ እንዲውል የተጠየቀው ገንዘብ በአስቸኳይ የማይገኝ ከሆነ በሶማሊያ ረሃብ እና በአፍሪካ ቀንድ የህጻናት ሞት ሊያሻቅብ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።

በአፍሪካ ቀንድ በተከታታይ አራት የዝናብ ወቅቶች ደርቀው ሲያልፉ ከ40 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ የታየ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ተብሎ ተመዝግቧል። ድርቁ የሚቀጥል ከሆነ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በአደገኛ ረሃብ ሊጠቁ እንደሚችሉ ገልጾ የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስጠንቅቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ በበኩሉ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ እና ሶማሊያ 1.7 ሚሊዮን ሕጻናት ሕይወታቸው ሊቀጥፍ በሚችል እጅግ የበረታ ረሃብ ውስጥ እንደሚገኙ በመግለፅ በአስቸኳይ መረዳት እንዳለባቸው ያሳስባል።

ፎቶ ፋይል - ከኢትዮጵያ ጎዴ ከተማ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሃርጉዶ የተባለ ቦታ በድርቅ ምክኒያት የሞቱ በጎችን ሰዎች ተሰብስበው እያዩ።
ፎቶ ፋይል - ከኢትዮጵያ ጎዴ ከተማ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሃርጉዶ የተባለ ቦታ በድርቅ ምክኒያት የሞቱ በጎችን ሰዎች ተሰብስበው እያዩ።

ራኒያ ዳጋሽ-ካማራ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የዩኒሴፍ ምክትል ኃላፊ ሲሆኑ ከኬንያ መዲና ናይሮቢ ሆነው ለቪኦኤ እንደተናገሩት አደጋው በተለይ በሶማሊያ የሚገኙና የአየር ለውጡ ዋና ተጠቂዎች በሆኑት ሕጻናት ላይ ይበረታል ብለዋል።

“በሶማሊያ 386,000 የሚሆኑ ሕጻናት ሞትን ሊያስከትል በሚችል ከፍተኛ የምግብ እጥረት ላይ በመሆናቸው አሁኑኑ መረዳት አለባቸው። በተመሳሳይ ረሃቡን 2011 ዓ.ም. ከነበረው ጋራ ስናነጻጽረው የተጎጂዎች ቁጥር ጨምሯል። በዚያ ዓመት ዕርዳታ የሚፈልጉት ሕጻናት ቁጥር 340,000 ነበር።”

እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣ2011 ዓ.ም. በሶማሊያ በነበረው ረሃብ ከሩብ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕጻናት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከነዚህ ውስጥ ግማሾቹ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ነው። ዳጋሽ-ካማራ እንደሚሉት ሕጻናት የሚሞቱት ረሃብ፣ ኩፍኝ እና ኮሌራ ተደራርበው ስለሚያጠቋቸው ነው። ድርቁ ሰብሎችንና እንስሳትን ሲያጠፋ የውሃ ምንጮችንም አድርቋል።

ሕጻናቱ በረሃብ በመጎዳታቸው እና በመድከማቸው ተያያዥም ሆነ ሌሎች በሽታዎችን መቋቋም አይችሉም።

ዳጋሽ-ካማራ አክለው እንዳሉት በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሕጻናት በዩክሬይን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያትም አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

“ሶማሊያን ብቻ ብንወስድ 92 በመቶ የሚሆነውን ስንዴ የምታስገባው ከሩሲያና ከዩክሬይን ነበር። አሁን ግን የአቅርቦት መስመሩ ዝግ ነው። ጦርነቱ በዓለም ላይ የምግብ እና ነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጓል። ስለዚህ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሰዎች በህይወት ለመቆየት እንኳን የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ የሆነ ምግብ ለማግኘት ውድ ይሆንባቸዋል።”

በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ ገንዘብ የለውም። ሕይወትን ለማትረፍ ለሚያከናውነው ሰብዓዊ ሥራ የሚያውለው መዋዕለ ንዋይ የለውም። የህጻናት ረድኤት ድርጅቱ ዩኒሴፍ ለአፍሪካ ቀንድ ከጠየቀው 250 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ያገኘው አንድ ሶስተኛውን ብቻ ነው። የዓለም የምግብ ፕሮግራም በበኩሉ በሶማሊያ የሚገኙ 4 ሚሊዮን ሰዎች ህይወትን ለመታድግ በሚቀጥሉት 6 ወራት 274 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል።

ድርጅቶቹ በወሩ መጨረሻ በጀርመን ስብሰባ የሚያደርገውንና G-7 በመባል የሚታወቀውን የሃያላን ሀገሮች ቡድን ዕርዳታ ተማጽነዋል። የእርዳታ ድርጅቶቹ እንደሚሉት የበለጸጉት የG-7 ሀገሮች መከሰት የሌለበትንና ሊከሰት የማይገባውን አደጋ ለመቀልበስ አቅሙ አላቸው።

/ዘገባው ሊሳ ሽላይን ነው። /

XS
SM
MD
LG