ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ በ10 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ቢወሰንም በፖሊስ ይግባኝ ምክንያት አልተፈቱም።
የዋስትና ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ዛሬ ተሰይሞ የነበረው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት፤ የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ፣ “ገበያኑ” የተሰኘ የዩቲዩብ ሚዲያ መስራችና አዘጋጅ ሰለሞን ሹምዬ እና የ”ሮሃ” ዩቲዩብ ሚዲያ አዘጋጅ መዓዛ መሐመድ የአስር ሺህ ብር ዋስ አስይዘው እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ሆኖም ፖሊስ ዋስትናውን በመቃወም ይግባኝ በመጠየቁ ምክኒያት ከእስር ቤት አለመውጣታቸው ታውቋል፡፡ፍርድ ቤት ተገኝተው ችሎቱን የተከታተሉት ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ስለውሳኔው ለቪኦኤ ሲያብራሩ ዋስትና የተፈቀደላቸው ሦስቱ የሚዲያ ባለሞያዎች ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ የዋስትና ገንዘቡን በማስያዝ ከእስር ለመውጣት ሂደት ከጀመሩ በኋላ፣ ፖሊስ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረቡን ገልፀዋል፡፡
ከሰዓት በኋላ ይግባኙን ሰምቶ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ውሳኔ ለመከታተል፣ እስረኞቹ፣ ፖሊስ እና ጠበቆች ወደ ፍርድ ቤት ቢያመሩም “ዳኛ ባለመገኘቱ ምክንያት” ጉዳዩ እንዳልታየም አክለው ገልጸዋል፡፡በመሆኑም፣ ዳኛ የሚገባ ከሆነ ሂደቱ ነገ ሰኔ 1/2014 ዓ.ም እደሚታይ እና ውሳኔ እንደሚሰጥበት አቶ ሄኖክ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የ”ኢትዮፎረም” አዘጋጅ የነበረው የያየሰው ሽመልስ እና የ “ኢትዮ ንቃት” ዩቲዩብ ሚዲያ አዘጋጅ የሆነችው መስከረም አበራ የዋስትና ጥያቄ ግን ውድቅ ተደርጎ ለሁለተኛ ዙር የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ፖሊስ በሁለቱ ተጠርጣሪዎች መዝገቦች ላይ የሚያደርገውን ምርመራ አጠናቆ እንዲቀርብ ተጨማሪ ስድስት ቀናት ተፈቅዶለታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚዲያ ባለሙያዎች እስራት አሁንም ከተለያዩ አካላት ተቃውሞ እየገጠመው ነው፡፡
እንደአውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በ1908 ዓ.ም የተመሰረተው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለፕሬስ ነፃነት እንደሚሟገት የሚገልጸው “ናሺናል ፕሬስ ክለብ” የተባለ ድርጅት ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ “በግፍ የታሰሩ” ያላቸው የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡
"በኢትዮጵያ በፍጥነት እያሽቆለቆለ ያለው የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ አሳሳቢነቱ ባለፉት ቀናት እየተባባሰ ሄዷል” ያለው ድርጅቱ፣ በፕሬስ ሥራቸው ሕጋዊ ጥፋት ፈጽመዋል በሚል የተከሰሱ ጋዜጠኞች ለፍርድ ከመቅረባቸው በፊት መታሰራቸው፣ በቅርቡ የጸደቀውን የሀገሪቱን የሚዲያ ሕግ የሚቃረን ስለመሆኑ ገልጿል፡፡ ለዚህም “በሕገወጥ መንገድ የሚዲያ ባለሞያዎች ታስረዋል” በሚል ኢሰመኮ ከሰሞኑ ያወጣውን መግለጫ “ናሺናል ፕሬስ ክለብ” በማሳያነት አንስቷል፡፡ በመሆኑም “በህገወጥ መንገድ የታሰሩት ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሠራተኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን” ብሏል ድርጅቱ።
የሚዲያ ባለሞያዎች እስራት ከሌሎች የሀገር ውስጥና የውጭ አካላትም ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ እርምጃው ሕግ የማስከበር አካል መሆኑን ነው መንግስት የሚገልጸው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ "የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያናጉ እንዲሁም በብሄር እና በሀይማኖት ጉዳዮች ላይ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ የሚያሰራጩ” ያላቸውን 111 የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን ለይቶ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን መግለጹ አይዘነጋም፡፡
/ሙሉውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ/