በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“መንኪፖክስ” የተባለው ወረርሸኝ በ200 ሰዎች ላይ መገኘቱንየዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ


መንኪፖክስ የተባለው ቫይረስ በተመረመረው ሰው ውስጥ መገኘቱን የሚያሳይ ቲዩብ። በአውሮፓ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 22, 2022. የተወሰደ
መንኪፖክስ የተባለው ቫይረስ በተመረመረው ሰው ውስጥ መገኘቱን የሚያሳይ ቲዩብ። በአውሮፓ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 22, 2022. የተወሰደ

መንኪፖክስ የተባለው አዲስ ወረርሽኝ በሃያ ሃገሮች ውስጥ ባሉ ሁለት መቶ ሰዎች ላይ መገኘቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ። ድርጅቱ ሃገሮቹ ያወጧቸውን ሪፖርቶች ጠቅሶ ባወጣው መግለጫ ከዚህ በፊት በሸታው ታይቶባቸው በማይታወቅ ሃገሮች መገኘቱን ጠቁሟል። ወረርሽኙ መገታት የሚቻል ዓይነት እንደሆነም ገልፆ ውስን የሆነውን መድኃኒት እና ክትባት ፍትኃዊ በሆነ መንገድ ማከማቸትና ማሰራጨት እንደሚገባ አሳስቧል።

ድርጅቱ አርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ አሁን የተከሰተው ወረርሽኝ እንዴት ከአፍሪካ ውጪ ሊሰራጭ እንደቻለ ግልጽ እንዳልሆነ እና ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ጠቅሶ፤ “የበሽታ አምጪው ህዋስ ዘረ መል በመቀየሩ ምክንያት ለመሆኑ ግን ምንም ማስረጃ የለም” ብሏል።

በአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስራኤል፣ አውስትራሊያ እና በሌሎችም ሃገሮች በቅርቡ የታዩት የበሽታው ስርጭቶች በስፔን እና በቤልጂየም ተካሂደው ከነበሩ ሁለት የመዝናኛ ዝግጅቶች እና ከግብረ ስጋ ግንኙነት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ አንድ የጤና ድርጅቱ ከፍተኛ አማካሪ ተናግረው ነበር። ይህም በሽታው በመካከለኛውና ምዕራብ አፍሪካ ተገድቦ ሲሰራጭበት ከነበረው እና እንደ ዝንጀሮና ጦጣ ባሉ የዱር አውሬዎች ምክንያት ሲተላለፍበት ከነበረው መንገድ የተለየ እንደሆነ ታውቋል።

የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ እንዳመለከተው የዓለም ጤና ድርጅት ስርጭቱ 200 አካባቢ ነው ቢልም ቁጥሩ ከዛም በላይ ሊሆን እንደሚችል ከየሃገሮቹ የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ።

አርብ ዕለት የስፔን ባለስልጣኖች በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 98 መድረሱንና ከእነዚህም ውስጥ አንዷ ሴት እንደሆነች ይፋ ሲያደርጉ ሴቲቱ የተያዘችት መንገድ ወንዶች በበሽታው ከተያዙበት መንገድ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና እንዳለው ተናግረዋል። እንግሊዝ 16 አዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ስታሳውቅ በሀገሪቱ ያለውን ድምር ብዛት ወደ 106 አሳድጎታል። ፖርቹጋል ደግሞ 74 ሰዎች መያዛቸውን ይፋ አድርጋለች።

በእንግሊዝ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ካናዳ፣ አሜሪካና በሌሎቹም ሃገሮች ያሉ ሃኪሞች በሽታው በአብዛኛው እየተላለፈ ያለው የተመሳሳይ ፆታ ግንኙት እና ሁለቱንም ዓይነት ግንኙነት በሚያደርጉ ወንዶች ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን ሰዎቹ በበሽታው የተያዙት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት አድራጊዎች በመሆናቸው ብቻ አለመሆኑንና ወረርሽኙ የማይገታ ከሆነ ሌሎችንም ሰዎች ሊይዝ እንደሚችል ሃኪሞች አስጠንቅቀዋል።

የዓለም ጤና ድርጅቱ የወረርሸኝ እና ተላላፊ በሽታዎች ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ሲልቪ ብራያንድ እንዳሉት ደግሞ በአፍሪካ እንደታየው የበሽታው ስርጭት ሂደት ከሆነ አሁን እየታየ ያለው የወረርሽኝ ሂደት በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል ነው። ኃላፊው ጨምረውም እንግሊዝ፣ ጀርመንና ካናዳ የፈንጣጣ ክትባትን መንኪፖክስ ተብሎ የተጠራውን ወረርሽኝ ለመግታት የሚውልበትን መንገድ እያጠኑ መሆኑንና የጤና ድርጅቱ በቅርቡ ጉዳዩን በተመለከተ መመሪያ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ሌላው የጤና ድርጅቱ የፈንጣጣ ክፍል ሃላፊ በበኩላቸው ደግሞ በአሁኑ ወቅተ ለሁሉም ሰው ክትባት መስጠቱ አስፈላጊ እንዳልሆነና መንኪፖክስ በቀላሉ የሚተላለፍ በሽታ አለመሆኑን እንዲሁም በሽታው ለመተላለፍ አንድ ሰው ከሌላው ሰው ጋ ከተነካካ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። ለመንኪፖክስ የተለየ ክትባት ባይኖርም የዓለም ጤና ድርጅት ግን የፈንጣጣ ክትባት ቢሰጥ 85% ውጤታማ እንደሆነ ግምቱን አስቀምጧል።

አብዛኛው የመንኪፖክስ ተጠቂዎች ትኩሳት፣ ቁርጥማት፣ ብርድ ብርድ ማለትና ድካም ሲታይባቸው፤ በጣም የጠናባቸው ደግሞ ፊትና እጃችው ላይ ሽፍታና ቁስል ሊታይባቸውና ይህም ወደ ሌሎች የሰውነታቸው ክፍል ሊተላለፍ ይችላል።

XS
SM
MD
LG