በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ ጋዜጣ የሌለባት ሀገር እንዳትሆን ያሰጋል 


ኢትዮጵያ ጋዜጣ የሌለባት ሀገር እንዳትሆን ያሰጋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:40 0:00

ኢትዮጵያ ጋዜጣ የሌለባት ሀገር እንዳትሆን ያሰጋል

በወረቀት ዋጋ መናር እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መንግስታዊው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በህትመት ዋጋ ላይ ከሰማኒያ ከመቶ በላይ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ የጋዜጦች ዋጋ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው አሳታሚዎች እና ጋዜጣ አዟሪዎች ተናግረዋል። የዋጋ ጭማሪው በጋዜጦችና መፅሄቶች የገፅ ብዛት እና የስርጭት መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ እያደረገ ሲሆን በዚህ ከቀጠለ ሀገሪቱ ጋዜጣ የማይታተምባት ሀገር ለመሆን እንደሚያሰጋት የሙያው ተንታኞች ተናግረዋል።

ከአራት አመት በፊት ከፍተኛ ዋጋ ኖሮት ሰባት ብር ከሀምሳ ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ሪፖርተር ጋዜጣ በየግዜው ዋጋ እየጨምረ ሄዶ ከሁለት ሳምንት በፊት 20 ብር ገብቷል። 6 ብር ከሀምሳ ሳንቲም የነበሩት ካፒታል እና ፎርቹን ጋዜጣም አሁን ዋጋቸው 20 ብር ነው። ከ15 እስከ 20 ብር ይሸጡ የነበሩ እንደ ፍትህ፣ ሀበሻ እና ግዮን የመሳሰሉ መፅሄቶችም እንዲሁ 25 ብር ገብተዋል።

በግል ጋዜጦች እና መፅሄቶች ላይ የታየው ይህ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ዋና ምክንያቱ የመንግስት የህትመት ተቋም የሆነው ብርሃን እና ሰላም በህትመት ዋጋ ላይ ከ80 በመቶ ጀምሮ ጭማሪ ማድረጉን ለአሳታሚዎች በላከው ደብዳቤ በማስወቁ እንደሆነ የቁምነገር መፅሄት ዋና አዘጋጅ እና የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምራት ሀይሉ ገልፀዋል።

አቶ ታምራት እንደሚሉት ጋዜጦች እና መፅሄቶች ከእጥፍ በላይ የሆነ የዋጋ ጭማሪ አድርገውም የህትመት ዋጋቸውን ለመሸፈን አይችሉም።

የህትመት ዋጋ መናር በሀገር ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች እና መፅሄቶች ዋጋ እንዲጨምር ከማድረጉ በተጨማሪ የገፅ ብዛታቸው እና የስርጭት መጠናቸው በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል። ለምሳሌ 48 ገፅ የነበረው የቁምነገር መፅሄት አሁን ወደ 28 ገፅ መውረዱንና በየሳምንቱ የነበረው ህትመትም ወርሃዊ እንዲሆን መደረጉን አቶ ታምራት ነግረውናል።

እንዲህም ሆኖ ዋጋውን ተቋቁመው ገበያ ላይ መቆየት የቻሉት ስድስት የግል ጋዜጦች እና አራት ወይም አምስት የሚሆኑ መፅሄቶች መሆናቸውን ላለፉት 10 አመታት በጋዜጣ አዟሪነት የሰራው ሙላቱ አየነ ይናገራል። በርካታ የስፖርት ጋዜጦችን ጨምሮ ሌሎቹ ከገበያ ውጪ ሆነዋል።

ሙላቱ ጋዜጣ በመሸጥ መተዳደር ሲጀምር በሳምንት ከ500 እስከ 600 ድረስ ገቢ ያገኝ እንደነበር ይናገራል። አሁን ግን በዋጋ ጭማሪው የተማረሩ አንባቢዎች መግዛት በመቀነሳቸው ኑሮውን መደጎም አቅቶታል።

ልክ እንደሱ አዲስ አበባ ውስጥ ጋዜጣ በማዞር የሚተዳደሩ ወደ 120 የሚጠጉ ወጣቶች አሉ የሚለው ሙላቱ የጋዜጦች እና መፅሄቶች ዋጋ ያደረሰባቸውን ተፅእኖ እንዲህ ይገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ መኩሪያ መካሻ ታዲያ ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ ሀገሪቱ ጋዜጣ የሌለባት ሀገር እንዳትሆን ያሰጋል ይላሉ።

ይህን ስጋት ለመቅረፍና የጋዜጦችና የህትመት ዋጋዎችን ህልውና ለመታደግ ወረቀት ከቀረጥ ነፃ ሆኖ እንዲገባ፣ የመንግስት ማስታወቂያዎች ለግል አሳታሚዎችም እንዲሰጥ እና መንግስታዊ ያልሆኑ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተቋማት ለዘርፉ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንዲፈቀድ ባለሙያዎቹ ጠይቀዋል።

XS
SM
MD
LG