በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሕወሓት በምህረት "እለቃቸዋለሁ" ያላቸው ምርኮኞች፣ አብዛኛው የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዳልሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ


የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መለዮ
የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መለዮ

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፣ ሕወሓት የአማራና አፋር አካባቢዎችን በሃይል ወረራ ስር አደርጎ በቆየባቸው ወቅቶች “በግዳጅ ይዞ ኢሰብአዊ ተግባራትን ሲፈጽምባቸው የነበሩ” ያላቸውን ሰዎች፣ “ለራሱ ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ለማዋል ምርኮኛ በማለት የሃገር ውስጥና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማጭበርበር እየሞከረ ነው” ብሏል።

መግለጫው አክሎም “የሽብር ቡድን” ባለው በሕወሓት ኃይል ‘ምርኮኞች ናቸው’ ተብለው የተለቀቁት አብዛኞቹ ዜጎች “የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ በወጣበት ወቅት ታግተው የቀሩ የሰራዊቱ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ታውቋል“ ብሏል።

በተጨማሪም ከልዩ ልዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ለስራ ትግራይ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ እና በሕወሓት እገታ ስር እንደቆዩ የተገለጹ “ሲቪል ነዋሪዎች” የመከላከያንና የተለያዩ ጸጥታ ሃይሎችን መለዮ በማልበስ “በምርኮኛ ስም ተሰልፈዋል” ከተባሉት መካከል መሆናቸውን፣ መንግስት እያደረገ ባለው ማጣራት ማረጋገጡን ነው መግለጫው ያመለከተው፡፡

የትግራይ ክልል የምርኮኞች ማዕከል አስተባባሪ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ብርሃነ ከበደ ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 11/ 2014 ዓ.ም መቀሌ ለሚገኘው የቪኦኤ ሪፖርተር ሙሉጌታ አፅብሃ በሰጡት ቃል፣ ከአራት ሺሕ በላይ ምርኮኞች እንደሚለቀቁ ተናግረዋል፡፡

“ወታደሮቹ የትግራይ ኃይሎች እስከሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች በመኪና እንደሚሄዱና ቀጣይ ጉዟቸው ደግሞ ከዓለምአቀፍ ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር እንደሚሆን” አቶ ብርሃነ ቢገልጹም፣ ዓለምአቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በበኩሉ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሣትፎ እንደሌለው አስታውቋል። ስለጉዳዩቪኦኤ የጠየቃቸው የኮሚቴው የአዲስ አበባ ቢሮ የኮምዩኒኬሽንስ ኃላፊ ፓትሪክ ሜዤቫንድ “ክልሉ የተማረኩ የፌደራል መንግሥት ወታደሮችን ለመልቀቅ መወሰኑን እንዳሳወቀ የሰሙት ከማኅበራዊ ሚዲያ መሆኑን” ገልጸው፣ “ዓለምአቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በዚህ ሥራ ተሣታፊ አለመሆኑንም" ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል የውጭ ግንኙነት ቢሮ አስተባባሪ መሆናቸውን የሚናገሩት ካናዳ የሚገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አቶ ዮሃንስ አብርሃ “ምርኮኞች በሚለቀቁበት ጊዜ እንደ ቀይ መስቀል ወይም ሌላ ዓለምአቀፍ ተቋም ትብብር ውጪ ሊደረግ እንደማይችል” ገልፀው ነገር ምን ዓይነት ክፍተት እንደተፈጠረ መቀሌ ከሚገኙት ባለሥልጣናት አጣርተው ምላሽ እንደሚሰጡ ነው የተናገሩት።ይሁን እንጂ የመንግስት ኮሙኒኬሽንበዛሬው መግለጫው “የፕሮፖጋንዳ ድራማ” ያለውን ይህን ድርጊት፣ ሕወሓት አሁን ላይ “የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ” ብሎ በማሰብ እንዳደረገው ገልጿል፡፡

ሕወሓት “በሃሰት ፕሮፖጋንዳ አሰልፎት ነበረ” ያለው ድጋፍ መቀዛቀዙን ያመለከተው መግለጫው፣ በመሆኑም “የዓለምአቀፉን ማህበረሰብ ልብ እገዛበታለሁ ያለውን የምርኮኞችን መፈታት አጀንዳ ለማድረግ እየሞከረ ነው” ሲል አብራርቷል። በዚህም “ሰላም ፈላጊ መስሎ ለመቅረብ” እየሞከረ እንደሆነ ነው የጠቆመው፡፡ ይህም የሕወሓት ቡድን ራሱን “ለጦርነት እያዘጋጀ” ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ነው ብሏል የመንግስት ኮሙኒኬሽን መግለጫ።

መግለጫው ነንግስት ሸኔ ከሚለው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው እንዲሁም ፅንፈኛ ተብለው ከተገለጹ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ሕወሓት አባላትን በመመልመል “ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ሰርጎ ገብ” የተባሉ ኃይሎችንም በምርኮኛ ስም አደራጅቶ “የእኩይ ተልእኮው ማስፈጸሚያና መረጃ መቀበያ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመንግስት በኩል የተደረገው ማጣራት አመልክቷል” ሲልም መግለጫው ይከሳል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ዙሪያ፣ ከመስሪያ ቤቱ ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ግን በትዊተር አድረሻቸው በሰጡት ምላሽ የመንግስት ኮሙኒኬሽንን መግለጫ ምርኮኞቹ መለቀቃቸውን የመካድ እርምጃ እንደሆነ አመለክተው ገና የተለቀቁትን ሁለት እጥፍ የሚያAክሉ ምርኮኞች በትግራይ ኃይሎች እጅ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG