በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 ተመድ ሶሪያን  እስረኞችን በምህረት ለመፍታት ማቀዷን አወደሰ


በእስር ቤቶች ውስጥ የቆዩ ዘመዶቻቸውን መፈታት የሚጠባበቁ ሶሪያዊያን፣ ደማስቆ ፣ ግንቦት 3/2022
በእስር ቤቶች ውስጥ የቆዩ ዘመዶቻቸውን መፈታት የሚጠባበቁ ሶሪያዊያን፣ ደማስቆ ፣ ግንቦት 3/2022

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ልዑክ ጌር ፔደርሰን በሺዎች የሚቆጠሩ በሽብር ክስ ጥፈተኛ ተብለው የታሰሩ ሶሪያዊያንን በምህረት ለመልቀቅ ሀገሪቱ ይፋ ያደረገችውን ዕቅድ በበጎ እንደሚቀበሉት በዛሬው ዕለት አስታውቀዋል።

ፕሬዚደንት ባሺር አል አሳድ ሀገሪቱን ባወደመው ፣ 11 ዓመታትን የፈጀ ጦርነት ወቅት በተደጋጋሚ የምህረት አዋጅ አስነግረዋል። በሚያዚያ ወር የተሰማው አዋጅ ግን ከሽብር ወንጀል ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎችን በተመለከተ ግጭቱ ከጀመረባቸው ጊዜያት ወዲህ ከወጡት ሁሉ በእጅጉ የተሟላ ይዘት ያለው እንደሆነ የለውጥ አቀንቃኞች ተናግረዋል።

ፔደርሰን ከሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋይሰል ሜክዳድ ጋር ስብሰባ ከተቀመጡ በኃላ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ፣ ምህረቱን ትግበራ ሂደት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደሚጠባበቁ ተናግረዋል። የምህረት ዕቅዱ( ሁኔታዎችን በማስተካከል ረገድ) አቅም አለው ብለው እንደሚያምኑ እና ማደግ የሚችል መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሚያዚያ ወሩ አዋጅ የሰዎችን ሞት ካስከተሉት ውጪ በሽብርተኝነት ወንጀል ለተከሰሱት ሁሉ ጥቅል ምህረት አድርጓል።የሶሪያ የፍትህ ሚኒስቴር በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች እንደተፈቱ አስታውቀዋል። የጦር ባለስልጣን የሆኑት አህመድ ቶታዘን በበኩላቸው ምህረቱ ተፈላጊ በነበሩ ነገር ግን ያልተያዙ ሰዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደሚያካትት ተናግረዋል። እሳቸው የተፈቱት ሰዎች ቁጥር በየሰዓቱ እንደሚለዋወጥ ከመጥቀስ ወዲያ እስካሁን የተፈቱትን ሰዎች ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የሶሪያ ሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ የተባለው ተቋም እስከ አሁን 1142 ሰዎች መፈታታቸውን አስታውቋል። በቀጣይ ጥቂት ቀናት በሶሪያ ውስጥ ሲፋለሙ የቆዩት አካላት የህገ-መንግስት ማሻሻያን በተመለከተ ሲውዘርላንድ ውስጥ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፔደርሰን የአሁኑ ስብሰባ መተማመንን የሚገነቡ እርምጃዎች እንዲታዩ የሚያግዝ አወንታዊ ጉባኤ ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ዘገባው የኤኤፍፒ ነው።

XS
SM
MD
LG