የፖላንድ ፕሬዚደንት አንድሬዚች ዱዳ በዛሬው ዕለት በዩክሬን ፓርላማ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ይሄም ከሩሲያ ወረራ በኀላ በዩክሬን ፓርላማ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ መጀመረው የውጭ ሀገር ርዕሰ- መንግስት ያደርጋቸዋል ። ፖላንድ እስከ አሁን ድረስ ከ2 ሚሊየን በላይ ዩክሬናዊያን ስደተኞችን ተቀብላለች ።
ይህ በእንዲህ እያለ ፣ ሩሲያ በዩክሬን ሉሃንሳክ ክፍለ ሀገር ጥቃቷን በበረታችበት በአሁኑ ሰዓት ከሀገሪቱ ጋር የተኩስ ማቆምም ሆነ በሌላኛው ወገን የቀረበ ጥያቄን በመቀበል ረገድ መግባባት ላይ ሊደርስ አለመቻሉን የዩክሬን ዋነኛ ተደራዳሪ በትናንትናው ዕለት አስታውቀዋል ።ሉሃንሳክ በምስራቅ ዩክሬን የሚገኘውን ዶንባስን ከፈጠሩ ሁለት ክፍላተ ሀገራት መካከል አንዱ ነው።
ከዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ መስሪያቤት ኃላፊ ሎይድ ኦውስቲን እና የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ የቀረቡ የተኩስ አቁም ጥያቄዎችን በተመለከተ መልስ የሰጡት ሚካሄሎ ፖዶላይክ ( የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎድሜር ዘለንስኪ አማካሪም ናቸው) ጦርነቱ ከባለንጣዎች ወገን የቀረቡ ጥያቄዎች ላይ መግባባት ቢደረስ እንኳ በጊዚያዊነት እንጂ ለዘለቄታው የማይቆምም መሆኑን ጠቁመዋል። “(ሩሲያዊያን) ከዚህ የባሰ ደም አፋሳሽ እና የገዘፈ አዲስ ጥቃት ይከፍታሉ” -ሲሉም አክለዋል።
ሩሲያ ክሪሚያን ከተቆጣጠችበት ከ2014 እኤአ ጀምሮ፣ አፍቃሪ ሩሲያ የሆኑ ተገንጣይ ኃይሎች፣ ሉሃንሳክ እና ዶንቴስክን ለመቆጣጠር ከዩክሬን ጋር ሲፋለሙ ቆይተዋል።
በሁለቱ ክፈለ-ግዛቶች በየሚገኙ የዩክሬን ኃይሎች በፌስቡክ ገጻቸው በኩል ይፋ እንዳደረጉት ፣ ሩሲያ በአየር ተዋጊዎች ፣ መድፍ ፣ ታንክ ፣ ሮኬት፣እና ሚሳኤሎችን ተጠቅማ የህዝብ መጠቀሚያ ተቋማት እና የመኖሪያ ስፍራዎችን በደበደበችባቸው ያለፉት 24 ሰዓታት ቢያንስ 7 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርገዋል-እንደ ሮይተርስ ዘገባ።
ዩክሬናዊያን 9 ጥቃቶችን ማክሸፋቸውን፣ 5 ታንኮች እና 10 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ማወደማቸውን በዚሁ የፌስቡክ መግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል። በዶንባስ ቀጠና ያለው ሁኔታ በእጅጉ አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆሙት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ቭሎድሜር ዘለንስኪ ፣ የሀገራቸው የሩሲያ ጦር ስሎቪያንሳክ እና ሺቨርኖንቴስክ የተባሉ ከተሞችን ለመቆጣጠር ያደረገውን ጥረት እንደመከተ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ሩሲያ ለዩክሬን ድጋፍ ያደርጋሉ ባለቻቸው ቀደ 1000 በሚጠጉ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች ላይ ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ቋሚ ገደብ ጥላለች።ከእነዚህ መካከል ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ፣ ምክትላቸው ካምላ ሃሪስ እንዲሁም የፕሬዚደንቱ ካቢኔት አባላት ይገኙበታል።