በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቀይ መስቀል ኮሚቴ ስለተለቀቁ ምርኮኞች እንደማያውቅ አስታወቀ


የቀይ መስቀል አርማ
የቀይ መስቀል አርማ

ትግራይ ክልልን እያስተዳደሩ ያሉት ባለሥልጣናት ሰሞኑን ይፋ ባደረጉት የፌደራሉን መንግሥት የጦር ምርኮኞች የመልቀቅ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሣትፎ እንደሌለው ዓለምአቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታውቋል።

የኮሚቴው የአዲስ አበባ ቢሮ የኮምዩኒኬሽንስ ኃላፊ ፓትሪክ ሜዤቫንድ “ክልሉ የተማረኩ የፌደራል መንግሥት ወታደሮችን ለመልቀቅ መወሰኑን እንዳሳወቀ የሰሙት ከማኅበራዊ ሚዲያ መሆኑን” ገልፀዋል።

በክልሉ የምርኮኞች ማዕከል አስተባባሪ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ብርሃነ ከበደ ከትናንት በስተያ ሐሙስ ግንቦት 11/ 2014 ዓ.ም መቀሌ ለሚገኘው የቪኦኤ ሪፖርተር ሙሉጌታ አፅብሃ በሰጡት ቃል ከአራት ሺሕ በላይ ምርኮኞች እንደሚለቀቁ የተናገሩ ሲሆን ሪፖርተራችን የክልሉ መንግሥት “ምርኮኛ ወታደሮች ናቸው” ያላቸውን ሰዎች ለመሸኘት በሚል መቀሌ ውስጥ በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቷል።

“ወታደሮቹ የትግራይ ኃይሎች እስከሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች በመኪና እንደሚሄዱና ቀጣይ ጉዟቸው ደግሞ ከዓለምአቀፍ ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር እንደሚሆን” አቶ ብርሃነ መግለፃቸውን አስመልክቶ ከቪኦኤ ለቀረበላቸው ጥያቄ አዲስ አበባ የሚገኙት የኮሚቴው ቃል አቀባይ ሜዤባንድ "ላረጋግጥልህ የምችለው ዓለምአቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በዚህ ሥራ ተሣታፊ አለመሆኑን ነው" ብለዋል።

የትግራይ ክልል የውጭ ግንኙነት ቢሮ አስተባባሪ መሆናቸውን የሚናገሩት ካናዳ የሚገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አቶ ዮሃንስ አብርሃ “ምርኮኞች በሚለቀቁበት ጊዜ እንደ ቀይ መስቀል ወይም ሌላ ዓለምአቀፍ ተቋም ትብብር ውጪ ሊደረግ እንደማይችል” ገልፀው ነገር ምን ዓይነት ክፍተት እንደተፈጠረ መቀሌ ከሚገኙት ባለሥልጣናት አጣርተው ምላሽ እንደሚሰጡ ገልፀውልናል።

በሌላ በኩል ደግሞ “የትግራይ ኃይሎች የምህረት መርኃግብር አካል በሆነ እርምጃ ከ4 ሺህ በላይ የጦር ምርኮኞችን መልቀቃቸውን” የህወሃት ቃል አቀባይ ትዊት ያደረጉትን መግለጫ ጠቅሶ አሶሼትድ ፕረስ ትናንት፤ ዓርብ ዘግቧል።

ህወሃት እሥረኞቹን መልቀቁን ያስታወቀው በትግራይ ክልልና በፌደራሉ መንግሥት ባለሥልጣናት መካከል የተጋጋሉ ቃላት መለዋወጥ እየተሰማ ባለበትና ትንኮሳ እና ለአዲስ ግጭት ሊያገረሽ ይችላል የሚል ሥጋት በበረታበት ወቅት ነው።

መሸኘታቸው ከተነገረው ምርኮኞች መካከል 401ዱ ሴቶች መሆናቸውን የህወሃቱ ቃል አቀባይ ያሠራጩት መግለጫ አመልክቷል።

አብዛኞቹ ወታደሮች የተማረኩት ከትግራይ ክልል ውጪ ነበሩ ውጊያዎች መሆኑን የምርኮኞቹ ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ብርሃነ ከበደ የገለፁ ሲሆን “ወደ ጦርነት እንዲሄዱ በግዳጅ የተቀላቀሉም ይገኙባቸዋል” ብለዋል።

የመንግሥቱን ቀጥተኛ ምላሽ ለማግኘት ወደ ቃል አቀባዮቹ ካደረግናቸው ብርቱና ተከታታይ ጥረቶች በኋላ ያገኘናቸው የኮምዩኒኬሽንስ ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልፀውልን በጉዳዩ ላይ መረጃ እየተሰባሰበ መሆኑንና ሲጠናቀቅ መንግሥት መረጃ እንደሚሰጥ” ነግረውናል።

ምርኮኞቹን የመልቀቅ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በሁለቱ ወገኖች የጦር አመራሮች መካከል ለሣምንታት በተደረገ ንግግር መሆኑን አሶሽየትድ ፕረስ ‘አዲስ አበባ ናቸው’ ያላቸውን አንድ ዲፕሎማት ጠቅሶ የዘገበ ሲሆን በፖለቲካ መሪዎች ደረጃ ግን እስካሁን ግንኙነት አለመደረጉን እንደነገሩት አመልክቷል።

ምርኮኞቹ ሲለቀቁ የአካል ጉዳተኞች፣ ታማሚዎችና ታስረው በነበሩበት ጊዜ የወለዱ ሴቶች ቅድሚያ እንደተሰጣቸውም ዲፕሎማቱ መናገራቸውን ኤፒ ጠቁሟል።

ባለፈው ሐምሌም አንድ ሺህ ምርኮኞችን ለቅቀው እንደነበረ በዓለም አቀፉ የቀውሶች ቃኚ ቡድን /አይሲጂ/ ውስጥ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከፍተኛ ተንታኝ ዊሊያም ዴቪሰን "ምርኮኞቹን የመልቀቁ ሂደት ምናልባት መልካም ፈቃደኛነታቸውንም በትግራይ ከፍተኛ የምግብ እጥረት መኖሩንም የሚጠቁም ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

XS
SM
MD
LG