በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ተወካይ የኢዮጵያ ቆይታ


የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ተወካይ የኢዮጵያ ቆይታ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:34 0:00

የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ተወካይ የኢዮጵያ ቆይታ

የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ማነቆዎችን መቅረፍ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ተወካይ ገለጹ።

ልዩ ተወካዩ ኤሞን ጊልሞር በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሦስት ቀናት ጉብኝት ሲያጠናቅቁ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳይ በተጨማሪ በሰብዓዊ መብቶች እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ዙሪያም ከተለያዩ አካላት ጋር እንደተወያዩ አብራርተዋል።

ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከልዩ ተወካዩ ጋር ተገናኝተው በሰብዓዊ መብቶችጥሰቶች እና በሰላም ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን የገለጹት የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደምም አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

ከሰኞ ግንቦት 8/2014 ጀምሮ እስከ ረቡዕ በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ቆይታ የነበራቸው የአውሮፓ ሕብረት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ተወካይ ኤሞን ጊልሞር፣ ትናንት ምሽት በሰጡት መግለጫ ከፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ከምክትል ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል፡፡ በተጨማሪም ከፍትሕ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ ከሲቪል ማህበረሰብ አባላት፣ ከሰብዓዊ ድርጅቶች፣ ከተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ፣ ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴኦየ እና ሌሎች በርካታ አካላት ጋር መወያየታቸውን አብራርተዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ያመሩት፣ በቀጣይነት በ27ቱ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት መካከል “በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በብራሰልስ ይደረጋሉ” ካሏቸው ስብሰባዎች በፊት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ በተስተዋሉ ለውጦች ዙሪያ እንዲሁም ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ቀጣይ ግንኙነት ዙሪያ ለመወያየት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ሚስተር ጊልሞር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ያደረጉባቸው ጉዳዮች ሦስት ሲሆኑ፣ እነርሱም የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሊደረግ የታቀደው ብሔራዊ ምክክርና በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የሚመራው የሰላም ሂደት፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች እና ተጠያቂነት ጉዳይ ናቸው፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን በተመለከተ ስላደረጉት ውይይት ሲያብራሩ፣ ምንም እንኳን ለሰብዓዊነት በሚል ግጭት የማቆም ውሳኔ ላይ ቢደረሰም አሁንም ድረስ ወደ ትግራይ ክልል በሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ችግሮች እንደሚስተዋለበት ገልፀዋል፡፡

የችግሮቹ መንስዔዎች “የተወሰኑት አስተዳደራዊ ፣ አንዳንዱ ቴክኒካዊና ከግለሰቦች ጋር የሚያያዙ የተወሰኑት ደግሞ ከአቅርቦት መስመር ጋር የተገናኙ ናቸው” ያሉት ሚስተር ጊልሞር፣ ይህንንም በውይይታቸው ወቅት ለኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ማሳወቃቸውን እና በጎ ምላሽ ማግኘታቸውንም አንስተዋል፡፡ ችግሮቹ እንደሚቀረፉ ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ጉዳይ የፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል አስተዳደር የሚወነጃጀሉበት ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሰብዓዊ አቅርቦቱ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አንጻር መሻሸሎች ስለመኖራቸው የተለያዩ የረድዔት ድርጅቶች ይገልጻሉ፡፡

በትግራይ ክልል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአስከፊ የምግብ እጦት ችግር ላይ እንደሚገኙ የሚያመለክቱት እነዚሁ አካላት፣ በመንግስት በኩል የተደረጉ ማሻሻያዎች ቢኖሩም የሰብዓዊ ድጋፉን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ይበልጥ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

የነበራቸው የአውሮፓ ሕብረት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ተወካይ ኤሞን ጊልሞር፣ ለሰላም የሚደረገውን ብሔራዊ ምክክር እና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ የሚያደርጉትን የሰላም ጥረት በተመለከተ ደግሞ፣ እነዚህን የሰላም ሂደቶች ሕብረቱ በቅርበት እንደሚከታተል እና ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በትናንት ምሽቱ መግለጫቸው አብራርተዋል፡፡ ምክክሩ አካታች የመሆኑ ጉዳይ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ እና በተለይ ሴቶች ጉልህ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ የተለያዩ ተሞክሮዎችን በማንሳት ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሰብዓዊ መብት እና ተጠያቂነት ጋር በተያያዘ ደግሞ፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት እጅግ አስደንጋጭ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን በመግለጽ፣ በኢሰመኮ እና በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ የተካሔደው የጋራ ምርመራና ሪፖርት በአውሮፓ ሕብረት ተቀባይነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በጥምር ሪፖርቱ የተሰጡ ምክረሀሰቦች ወደ ተግባር ሊቀየሩ እነደሚገባና ተጠያቂነት መረጋገጥ እንዳለበት በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመውን ዓለም አቀፍ መርማሪ አካል፣ ኢትዮጵያ እንድትቀበል መጠየቃቸውን እና በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ አመራሮች ጋር መወያየታቸውን ቢገልጹም ስለተሰጣቸው ምላሽ ግን አልጠቀሱም፡፡

ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመውን የምርመራ አካል እንደማትቀበል በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወቃል፡፡ ሚስተር ጊልሞር ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት በሁለተኛው ቀን - ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 9፣ አቶ ደመቀ መኮንን ለተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅትም፣ ይህንኑ የኢትዮጵያን የጸና አቋም አንጸባርቀዋል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ያስቀመጡት፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ሊያካድ ያሰበው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ “ኢሰመኮ እና የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ከዚህ ቀደም ካደረጉት የምርመራ ይዘት ጋር ተመሳሳይ ነው” የሚል ነው፡፡

ኢትዮጵያ፣ ሁለቱ አካላት በጋራ ባወጡት ሪፖርት ያቀረቡትን ምክረሀሳብ ለመተግበር በእንቅስቃሴ ላይ ባለችበት ወቅት ተመሳሳይ ምርመራ ማድረግ ጥቅም እንደሌለውም የገለጹት አቶ ደመቀ፣የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ምንም ምርመራ ባልተደረገባቸው በአፋር እና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ከሆነ “ኢትዮጵያ ትብብር ታደርጋለች” ብለዋል፡፡ ኢሰመኮን እና የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ በጋራ ያወጡትን የምርመራ ሪፖርት ኢትዮጵያ (ከተወሰኑ ይዘቶቹ ውጭ) ስትቀበል፣ ሕወሓት እና የኤርትራ መንግስት ውድቅ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ባትቀበልም፣ የተባበሩትመንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን እና የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ላቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን፣ ሦስት አባላትን ሰይሞ ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው፡፡

XS
SM
MD
LG