በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሊንኪን በምግብ ዋስትና ዙሪያ በኒው ዮርክ የአፍሪካ ሚኒስትሮችን አነጋገሩ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

“በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት አማካኝነት የተገለጸው የጥናት ግኝት፣ ለከፍተኛው የምግብ ደህንነት ቀውስ ተጋላጭ ከሆኑ 39 አገራት መካከል 32ቱ በአፍሪካ እንደሚገኙ ያመለክታል” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ተናገሩ፡፡

ብሊንክን ይህን የተናገሩት በዓለም የምግብ ደህንነት ላይ ለመምከር በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ዛሬ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለመገኘት የመጡትን የአፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ከስብሰባው በፊት በትናንትናው ዕለት ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

ብሊንከን ቀደም ሲሉ የነበሩ ችግሮችን የሩሲያው የዩክሬን ጦርነት በማባባስ ከፍተኛውን ድርሻ መያዙንና 40 ሚሊዮን ህዝብ ለረሃብ አደጋ መጋለጡን ገልጸዋል፡፡

አገራቸው ለአፍሪካ አገሮች ለአፋጣኝ የምግብ እርዳታ የምትሰጠውን ተጨማሪ 215 ሚሊዮን ዶላር እርዳታም ይፋ አድርገዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት በሰጡት መግለጫ በስብሰባው ላይ የተገኙት የኮንጎ ዴሞክራቲ ሪፐብሊክ፣ የግብጽ፣ የጋቦን፣ የጋና፣ የኬንያ፣ የሞሪታኒያ፣ የናይጄሪያ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የዛምቢያ እና የሴንጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ብሊንከን ለሚኒስትሮቹ ባሰሙት ንግግር ዓለም አቀፍ የምግብ ደህንነቱ ስብሰባ፣ አፍሪካ ላይ ማተኮር እንዳለበት ሲገልጹ “በምግብ ደህንነት ጉዳይ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ውይይት በመላው አፍሪካ እየሆነ ባለው ነገር ላይ ማተኮር አለበት። እጅግ ከከበደው ሸክም ውስጥ አገሮቻችሁ የተወሰነውን ተሸክመዋል፣ ይህ የምናየውና የምንገነዘበው ነገር ነው” ብለዋል፡፡

“መፍትሄዎቹን አስመልከቶ የቱ እንደሚስራና የቱ እንደጎደለ ከናንተ በላይ ሊያውቅ የሚችል የለም” ያሉት ብሊንከን፣ አሁን ለሚታየው የምግብ ደህነንት ቀውስ መንሴዎቹ በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ “የኮቪድ-19 በምጣኔ ሃብቱ ላይ ያሳደረውን ቀውስ ጨምሮ፣ ሁላችንም በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰማን ያለውና አፍሪካውያን ለረጅም ጊዜ በቅርብ የሚያውቁት፣ እየተባባሰ የመጣው የአየር ንብረት ቀውስ” ይገኙበታል ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የዩሩሲያው የዩክሬን ወረራም እንዚህን ችግሮች በማባባስ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ በዓለም ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ለምግብ ደህንነት ዋስትና መጋለጡን አመልክተዋል፡፡

“በዓለም የምግብ እጥረት መኖሩንና የምግብ፣ የማዳበሪያና የነዳጅ ዋጋ መናሩን ተመልክተናል”ያሉት ብሊንከን፣ ለምግብ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጠችው አፍሪካ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

“በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት አማይካነት የተገለጸው የጥናት ግኝት ለከፍተኛው የምግብ ደህንነት ቀውስ ተጋላጭ ከሆኑ 39 አገራት መካከል 32ቱ በአፍሪካ እንደሚገኙ ያመለክታል፡፡” በማለትም ብሊክን የአደጋውን መጠን አስታውቀዋል፡፡

ብሊንከን ከዚህም ጋር አያይዘው ዩናይትድ ስቴትስ በዩክሬን ላይ የሚካሄደውን ይህን ትርጉም የለሽ ጦርነት ለማስቀረት፣ ከሩሲያ፣ ከአፍሪካ ህብረትን፣ የአውሮፓ ህብረትና የኔቶ አጋሮቻችን ጨምሮ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ሙከራዎችን ማድረጓን አስረድተዋል፡፡

ይህንን ሁሉ ተላልፋ ወረራውን በፈጸመችው ሩሲያ ላይ በተለያዩ አገሮች የተጣለው ማዕቀብ የማዳበሪያ፣ ዘርን ጨምር ምግብ ሸቀጦችንና ምርቶችን የማያጠቃላል ቢሆንም፣ ሩሲያ ግን ከዩክሬን የሚመረቱ ምርቶችን ሆን ብላ ወደ ውጭ እንዳይወጡ መከልከሏን ተናግረዋል፡፡

የዩክሬን የምግብ ማስተላለፊያ ወደቦችና መንገዶች በሩሲያ መደብደባቸውና፣ ብዙዎቹም የጦር አውድማ፣ ወይም ሰዎች አገር ለቀው የሚሰደዱባቸው ስፍራዎች መሆናቸውን ብሊንከን ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ በቆሎ፣ ስንዴ፣ የምግብ ዘይትና ሌሎች ተያያዥ ምርቶችን በመላክ ቀዳሚዋ የሆነቸው ዩክሬን፣ በዚህ ሁኔታው ውስጥ በመኖሯ፣ ዓለም በተለይም አፍሪካ በፕሬዚዳንት ፑቲን ምርጫ እየተሰቃየች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አያዘውም፣

“ስለዚህ ዛሬ እዚህ መገናኝታችንን ወሳኝ የሚያደርገው፣ ችግሩንና ዜጎቻችሁ እየተሰቃዩበት ያለውን አሰመልክቶ ምን ማድረግ እንደምንችል በቀጥታ ከናንተው ለመስማት እንድንችል ነው፡፡ ለምሳሌ በማዕቀቡ ሳቢያ አገሮች ወደእነሱ የሚገባው የምግብ ወይም ማዳበሪያ ፍሰት እንዳይቋረጥ ማረጋገጥ የምንችልበትን የተለየ መንገድ ካለ ማወቅ እንፈልጋለን፡፡ ለዚያ ድጋፍ አፋጣኝ እርዳታ ለማድረግ ዝግጁ ነን፡፡” ሲሉ የአገራቸውን አቋም ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ እየተደረገ ስላለውና ሊደረገው ስለታቀደውም ነገር ሲያብራሩ፣

“ለረጀም ጊዜ የሚሆን የግብርና አቅም መገንባት ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ እዚህ ላይ የአፍሪካ ልማት ባንክ 40ሚሊዮን የሚደርሱ አርሶ አደሮችን የአየር ንብረትን ለውጥን የሚቋቋሙ ቴክኖሎጂዎችንና ሰብሎችን ምርት ለማስፋፋት ያወጣውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ፕሮግራም አሰመልክቶ የሠራውን ትልቅ ሥራ ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡” ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ለመጭው 15 ዓመታት የምግብ ዋስትናን በማሻሻል ላይ ያተኮረ “መጭውን መመገብ” የተሰኘው ተነሳሽነት፣ በመላው አፍሪካ የሚገኙ አጋሮችን ጨምሮ በጋራ ተግባራዊ የሚደረግ የምግብ ዋስትና እቅድ መኖሩንም ብሊንክን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የተነሳሽነት እቅድም ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚሆን 5 ቢሊዮን ዶላር መመደቡንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

ይህ የዩናይትድ ስቴትስ ለምግብ ደህነነት ዋስትና የምትሰጠውን ትኩረት የሚያመልክት መሆኑን በመግለጽ፣ ካለፈው የካቲት ወዲህ እንኳ አገራቸው ለምግብ እርዳታ ተጨማሪ የ2.3 ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል መግብቷን አስረድተዋል፡፡

ለዓለም የምግብ ዋስትና በተለየ የምንሰጠውን 760 ሚሊዮን ዶላር ጨምሮ በጠቅላላው ለምግብ ዋስትና ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ እርዳታ እንሰጣለንም ብለዋል፡፡

በመጨረሻም “ዛሬ ለአፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚውል ተጨማሪ 215 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ የምንሰጣቸው መሆኑን ይፋ ከማደርጋቸው የአፍሪካ አገሮች መካከል፣ አልጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ዩጋንዳ፣ ዚምባቡዌ፣ ሞሪታኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያና ኬንያ ይገኙበታል” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን አስታውቀዋል፡፡

XS
SM
MD
LG