በሶማሌ ክልል ቦምባስ ከተማ መጋቢት 11 እና 12 በክልሉ ፀጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ግለሰቦች በተወሰደ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ 11 ሰዎች ሲሞቱ በትንሹ 33 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ አስታወቀ።
ድርጊቱ የተፈጸመው በክልሉ ፋፈን ዞን ጉርሱም ወረዳ ቦምባስ ከተማ በባሕላዊ ሥነ ሥርዓት የጎሳ መሪ (ሱልጣን) ለመምረጥ በተሰበሰቡ ሰዎችና በፀጥታ አካላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች የምርመራና ክትትል ስራ ክፍል ሪጅናል ዳይሬከተር አቶ ኢማድ አብዱልፈታህ ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ የተወሰደው እርምጃ ከመጠን ያለፈ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንም ማረጋገጣቸውን የተናገሩት አቶ ኢማድ፣ ለሟች ቤተሰቦች እና ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ካሳ ቢከፈልም ወንጀሉን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከሶማሌ ክልል የመንግስት አካል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡