በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል የተፈጥሮ አካባቢ ውድመት ሥጋት አለ


ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወታደር በኮምቦልቻ ኢትዮጵያ እአአ ታህሣስ 10/2021
ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወታደር በኮምቦልቻ ኢትዮጵያ እአአ ታህሣስ 10/2021

ትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነቱ የደን ምንጠራን እያባባሰ ነው ሲል አንድ ተቀማጭነቱ እንግሊዝ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ ቡድን አስጠነቀቀ።

በቂ ነዳጅና እርዳታ ወደ ክልሉ ባለመግባቱ የምግብ እጥረቱን እያባባሰው መሆኑንና የክልሉ ነዋሪዎች ዛፎችን ለመቁረጥ መገደዳቸውንም ቡድኑ ማስታወቁን ኮምበልቻ የሚገኘው ሪፖርተራችን ሄነሪ ዊልከንስ ከኮምቦልቻ ዘግቧል።

ጦርነት ወደ አደቀቃት ትግራይ ለዘጠኝ ወራት እርዳታ እንዳይገባ ታግዶ ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና ታጣቂዎችም እርዳታ እንዳይገባ በማድረግ እርስ በእርስ ይወነጃጀላሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በትግራይ የደረሰው የምግብ እጥረት ምክንያት እስከዛሬ ታይቶ የማያውቅ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል። የትግራይ ተወላጆች ለእለት ኑሮአቸው የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ለማግኘት ያለውን አማራጭ ሁሉ ይጠቀማሉ።

አንድ ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነና ግጭት ባለባቸው ሥፍራዎች የአካባቢ ሁኔታን የሚያጠና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያስያየው በትግራይ ያለው ጦርነት እና የእርዳታ ዕጦት በአካባቢ ላይ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን ለትግራይ ነዋሪዎች ለአስርት ዓመታት የሚቀጥል ችግር መሆኑን አመልክቷል።

ከትግራይ የሚወጡ የሳተላይት ምስሎችን በመመልከት የተሰራው ጥናትም 'ግጭት ያባባሰው የደን ጭፍጨፋ' በአስደንጋጭ ፍጥነት እየተካሄደ መሆኑን ያሳያል ይላል። ዛፎች አፈርንና ውሃን በመጠበቅ ምግብ በማምረት ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። የእርዳታ ተቋማት ደግሞ ትግራይ ውስጥ ሰዎች በረሃብ ቋፍ ላይ መሆናቸውን በመግለፅ አስጠንቅቀዋል።

ሄነሪክ ሹልቴ የጥናቱ ፀሃፊ እና ለንደን በሚገኘው ዙሎጂካል ሶሳይቲ የተሰኘ ተቋም የአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ ባለሙያ ሲሆኑ በግጭት ምክንያት የሚደርስ የደን ጭፍጨፋ የሚከሰተው በሁለት ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ።

"አንደኛው ምክንያት የአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ሲፈርስ ነው። ለምሳሌ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጥበቃ ይደረግላቸው የነበሩ አካባቢዎች ጥብቃ ሲያጡ ሰዎች ወደ አካባቢው በመግባት ዕፅዋትን ያነቅላሉ። በተጨማሪም ከውጭ ለሚመጡ ግብዓቶች ያለው ፍላጎት እየጨመረ በሄደ ቁጥር የደን ጭፍጨፋ ይካሄዳል።"

በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን የሚገኝ የአካባቢ ጥበቃ ምርምር የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም የአፍሪካ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ራፋዬል ኤዱ በበኩላቸው በአፍሪካ ዛፎች የሚጨፈጨፉት ገንዘብ ለማግኘት ነው ይላሉ።

"አፍሪካ ውስጥ ግጭቶች እና የደን ጭፍጨፋ ለማኅበረሰብ ልማት ትልቅ ሥጋት ናቸው። ህገ ወጥ የዛፍ ጭፍጨፋ በአቋራጭ ገንዘብ ከሚገኝባቸው መንገዶች አንዱ ነው። ደኖች ለታጣቂዎች መሳሪያ መግዣነትም እየዋሉ ነው። ሁልግዜም ደኖች ውስጥ የሚገኙ ዛፎችን እንደቆረጡ ነው።"

ኤዱ አክለውም ግጭት ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ከፍተኛ መጠን ያለው የደን ጭፍጨፋ እንደሚደርስ ያስረዳሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በትግራይ ደኖችን መልሶ በማልማት፣ የአካባቢውን ልማት ለመጠበቅ፣ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እና በምግብ ራስን ለማስቻል ስኬታማ ጥረቶች ተደርገዋል። ጥናቱ እንደሚያሳየው እነዛ ጥረቶች አሁን መሰናክል ገጥሟቸዋል። ሆኖም ለትግራይ ህዝቦች በአሁኑ ወቅት አሳሳቢው ጉዳይ በህይወት መቆየት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ፣ ትግራይን ጨምሮ በተወሰኑ የአፋር እና አማራ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ 9.4 ሚሊየን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ሹልቴ እንደሚሉት የደን ጭፍጨፋውን ለማስቆም ተመራጩ መንገድ ግጭቱን ማስቆም ነው። ያም ሆኖ ግን በአካባቢው ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማከም አስርት ዓመታት ሊፈጅ ይችላል።

XS
SM
MD
LG