የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ "በጦርነት የተወረሰ የትንሳዔ በዐል" ሲሉ በገለጹት ዕለት ዐለም ለክፋት እና ለብጥብጥ እንዳይንበረከክ ተማጽኖ አቅርበዋል። በዩክሬይን የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆም አጥብቀው ጥሪ አሰምተዋል።
ባለፉት ሁለት ዐመታት በኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሽኝ ምክንያት የቤተክርስቲያኒቱ ሳምንታዊ የቅዳሴ እና ስብከት ስነ ስርዐቶች ተቋረጠው ከርመዋል እና ለዘንድሮው የትንሳኤ በዐል ለታደሙት ምዕመናን የዛሬው በርግጥም የትንሳዔ ቀን ሆኖላቸዋል።
በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተካሄደው ስርዐተ ቅዳሴ በመካፈል የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን ቃለ ቡራኬ ለማዳመጥ በብዙ አስር ሺዎች የተቆጠሩ ምዕመናን ታድመዋል።
በጦርነት በወደመችው በዩክሬይን ሰላም መልሶ እንዲሰፍን አጥብቀው የተማጸኑት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያች ሀገር ያለውዴታዋ በገባችበት ትርጉም የለሽ ጦርነት ለከበደ ጉዳት ተዳርጋለች ብለዋል።
"ዐለም ጦርነትን መላመድ የለበትም፥ አዲስ የተስፋ ቀን ይምጣ፥ ለሰላም በቁርጠኝነት እንቁም ፥ ሰው እየተሰቃየ ጡንቻን ማሳየት ይብቃ" ያሉት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ " የዐለም መሪዎች የህዝቡን ተማጽኖ ይሰማሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።
በሌሎች በርካታ የዐለም አካባቢዎች ያሉት ግጭቶች የህዝብ ስቃይ እና ሀዘን መረሳት ወይም ችላ መባል እንደሌለባቸው የአውሮፓው ጦርነት ሊያስታወሰን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።