በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለአምነስቲና ለህዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ከባህር ዳርና ከመቀሌ የተሰጡ ምላሾች


አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዋች ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት በአማራ ክልል ባለሥልጣናትና በክልሉ ታጣቂ ቡድኖች በትግራይ ተወላጆች ላይ “ዘር የማፅዳት ጥቃት ተፈፅሟል” ሲሉ ያወጡትን የጋራ ሪፖርት “ሚዛናዊነት፣ ገለልተኛነትና ተዓማኒነት የሌለው” ሲል የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እንደማይቀበለውና እንደሚቃወመው ትናንት (ዕሁድ) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሪፖርቱን “የህዝባችንን ጩኸት ለመቀማት ያነገበ” ሲልም የክልሉ መንግሥት ከስሷል።

በሌላ በኩል እራሱን “የትግራይ የውጭ ጉዳዮች ቢሮ” ብሎ የሚጠራው አካል ዓርብ፤ መጋቢት 30/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “የትግራይ መንግሥት (ጋቨርንመንት ኦብ ትግራይ) ሲል የጠራው አካል ቡድኖቹ ላወጡት ሪፖርት ምሥጋና እንደሚያቀርብ አመልክቶች “የተጠቀሱት የጭካኔ አድራጎቶች በትግራይ ተወላጆች ላይ ከተፈፀመው እጅግ ጥቂቱ ናቸው” ብሏል።

ሪፖርቱና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አድራጎቶቹን “ዘር ማጥፋት” ብለው እንዲጠሩ መግለጫው ጎትጉቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ያካሄዱትን ምርመራ ውጤት ይፋ ባደረጉበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባሽሌት በሰጡት መግለጫ “ትግራይ ውስጥ የጦር ወንጀሎችና በሰብዕና ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ስለመኖራቸው” ተናግረው “ዘር ማጥፋት ተፈፅሟል ለማለት የሚያበቃ ማስረጃ ግን አላገኘንም” ማለታቸው ይታወሳል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ “ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ተፈፅመዋል የተባሉትና በሁለቱ ድርጅቶች ሪፖርት የተገለፁት የጭካኔ አድራጎቶች በብርቱ እንደሚያሳስቡት ጠቁሞ ህይወት አድን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያለገደብና ያለማቋረጥ እንዲደርስ እንዲደረግ ማሳሰቡ ተገልጿል።

የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀቦችን ከመጣል አንስቶ ከአፍሪካ የዕድገትና የዕድሎች ተጠቃሚነት ህግ (አጎአ) መርኃግብር እስከማስወጣት የደረሱ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ለአምነስቲና ለህዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ከባህር ዳርና ከመቀሌ የተሰጡ ምላሾች
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:20 0:00
XS
SM
MD
LG