የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ስቴም ሲነርጂ ከተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ከሚገኙ የመንግሥት ዩንቨርስቲዎች የተመረጡ እና የማኅበረሰቡን ችግር መቅረፍ በሚችሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራቸው ልዩ ብቃት ላሳዩ አስር ሴት ተማሪዎች ሽልማት አበርክቷል። ሽልማቱ በተለይ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚታየውን ፆታዊ አለመመጣጠን ለመቅረፍ እና እጅግ አናሳ የሆነውን የሴቶች ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚረዳም ተገልጿል።
ከጅማ ዩንቨርስቲ በኤሌክትሪካል እና ኮምፒውተር ኢንጅነሪንግ ዘንድሮ የተመረቀችው ሱማያ ሁሴን በአርባ ምንጭ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቷን ስትማር ጀምሮ ለሳይንስ ትምሕርቶችና ለቴክኖሎጂ ውጤቶች ልዩ ፍቅር እንደነበራት ታስታውሳለች። በትምህርት ቤቷ ውስጥ በነበረው የፈጠራ ክለብ የነበራት ተሳትፎም ለኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች የተለየ ትኩረት እንዲኖራት ረድቷታል። ሆኖም ከማኅበረሰቡ የሚደርስባት ተፅእኖ ግን ፈታኝ እንደነበር ታስታውሳለች።
ከሀዋሳ ዩንቨርስቲ ኮምፒውተር ሳይንስ የተመረቀችው ሳምራዊት ኢዛናም በቴክኖሌጂ ዘርፍ ለሰውሰራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) የነበራት ተሳትፎ በበርካቶች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል። በተለይ የመመረቂያ ፕሮጀክቷን በብዛት ወንድ ተማሪዎች የሚሰርቱን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት መወሰኗ 'ተይ ይቅርብሽ' የሚሉ ምክሮችን እንዳስከተለ ትናገራለች።
ለመሆኑ ሴት ተማሪዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምሕርት እንዳያድጉ የሚያግዳቸው ምንድ ነው? ስመኝሽ የቆየ በውድድሩ ያሸነፉ ተማሪዎችን አነጋግራ ያሰናዳችውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ።