በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የትምሕርት ድጋፍ በኩታበር


የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የትምሕርት ድጋፍ በኩታበር
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:56 0:00

የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የትምሕርት ድጋፍ በኩታበር

ሊያ እንዳለ ኢትዮጵያ ተወልዳ በአንድ አመቷ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ ካቀናች በኃላ ለአመታት አገሯን የማየት እድል አልገጠማትም። ሆኖም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች የተወዳደረችበትን የቁንጅና ውድድር አሸንፋ ምን መስራት እንደምትፈልግ ስትጠየቅ መልሷ "ትምህርት፣ በተለይ በተወለድኩባት ኢትዮጵያ፣ ለሁሉም በስፋት እንዲዳረስ ማድረግ" የሚል ነበር።

ሊያ የመጀመሪያ ዲግሪ ዩንቨርስቲ ትምህርቷን እየተማረች ለመጀምሪያ ግዜ ወደ ኢትዮጵያ በተጓዘችበት ወቅት አያቶቿ ይኖሩበት በነበረው አማራ ክልል፣ ኩታበር የተዋወቀችው ተማሪ ህልሟን ለመተግበር መነሻ ሆነ።

"መንገድ ላይ ስሄድ ሲከተለኝ ይታወቀኛል። ዞር ስል ይደበቃል። ከዛ ችግር የለም ና አብረኸኝ ሂድ አልኩት እና የት እንደሚኖር ጠየኩት። የነበርነው ተራራ ላይ ነበርና የሚኖረው አራት ተራራዎችን አልፎ እንደሆነ በእጁ እየጠቆመ አሳየኝ። እንዴት አርገህ እዚህ መጣህ ስለው ትምህርት ለመማር በእግሩ ተጉዞ እንደመጣ ነገረኝ። ይሄ ለኔ አይኔን የከፈተልኝ አጋጣሚ ነበር።"

ሊያ ከዚህ ጉዞዋ በኃላ ቤተሰቦቿን አስተባብራ በኩታበር አካባቢ የሚማሩ ተማሪዎች የሚጠቀሙበትና የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን የያዘ የትምህርት ማዕከል አቋቋመች። በአቅም ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን ላቋረጡ ወይም ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን መሳሪያዎች ማሟላት ላልቻሉት ደግሞ የገንዘብና የቁሳቁስ ርዳታ በማድረግ ትምህርታቸውን መቀጠል የሚያስችላቸውን ድጋፍ መስጠት ጀመረች ።

"የምንሰራው ዝም ብሎ ገንዘብ መስጠት እንዲሆን አልፈለግንም። ግን ተማሪዎቹ የምንሰጣቸውን ገንዘብ ተጨማሪ ገቢ በሚያመጣ መልኩ ተጠቅመው እንዴት ትምህርታቸውን ይደግፋሉ የሚለው ላይ ነው መስራት ይፈለግነው። ስለዚህ ተማሪዎቹ ፎርሞችን እንዲሞሉና ምን መስራት እንደሚፈልጉ ጠየቅናቸው። ከተመረጡት ተማሪዎች መካከል ለምሳሌ አንደኛዋ ወደ ደሴ በመሄድ እቃዎችን እያመጣች ለመንደሯ ገበያ በመሸጥ ገቢ ማግኘት ጀመረች። ሌላኛው ተማሪ ደግሞ ዶሮዎችን ገዝቶ ከእናቱ ጋር እያረቡ ዶሮ፣ እንቁላልና የትምሕርት መሳሪያዎችን ይሸጣሉ።"

ሊያ እነዚህን ርዳታዎች የምታካሂደው እ.አ.አ አማካኝነት በ2010 በመሰረተችው ዓለም አቀፍ የትምህርት ፋውንዴሽን አማካኝነት ሲሆን ፋውዴሽኑ የሚረዳቸው ተማሪዎች ትምርታቸውን ጨርሰው ሥራ እስከሚይዙ ድረስ በቋሚነት ድጋፍ ያደርግላቸዋል። እስካሁን ስምነት ተማሪዎችን ለስኬት ማብቃት እንደቻሉም ሊያ ትገልፃለች።

"ለምሳሌ የመጀመሪያው የረዳነው ተማሪ ምን መሆን እንደሚፈልግ አያውቅም ነበር። አሁን ተመርቆ ሌላ ከተማ ላይ አንስቲዝዮሎጂስት ሆኖ ያገለግላል። ሌላኛዋ የምንረዳት ተማሪ ዩንቨርስቲ ለመግባት ከቤተሰቧ መለየት ነበረባት ግን እራሷን የምትደግፍበት ገንዘብ አልነበራትም። ስለዚህ በምንረዳት ገንዘብ ስለምግቧ፣ ልብስ እና መፅሃፍ እንዳታስብ በማድረግ ትምህርቷን እንድትቀጥል ማድረግ ችለናል።"

ሊያ በኢትዮጵያ የገጠር ትምህርት ቤቶችን ከመደገፍ ባሻገር በአሜሪካ ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የአፍሪካ የዘር ግንድ ያላቸው ተማሪዎች ማንነታቸውን ባለመረዳት ምክንያት የሚደርስባቸውን ችግር ለመቅረፍ ለልምድ ልውውጥ የሚረዱ ጉዞዎችን ታዘጋጃለች።

"ብዙ ጥናቶች የሚያሳዩት አፍሪካዊ እሴቶች እና ባህልን ማዕከል ካደረጉ ስርዓቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ወይም ወደ አገራቸው መሄድ የቻሉ እና ስለተለያዩ ቦታዎች የሚያውቁ ተማሪዎች፣ በትምህርታቸው የተሻለ ተሳትፎ አላቸው፣ የተሻለ ውጤትም ያመጣሉ። ስነ ልቦናቸውም በተሻለ ሁኔታ የተገነባ ነው። ስለራሳቸው የተሻለ እውቀት ስለሚኖራቸው ከሰዎች ጋር ጤናማ የሆነ ግንኙነት ይኖራቸውል። ስለዚህ ያ እንዲሆን መንገዱን መፍጠር ነው ፍላጎቴ። ግን ሁለቱንም ማህበረሰብ በሚጠቅም መልኩ።"

በዚህ መልኩ ሊያ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያየ የአፍሪካ የዘር ግንድ ያላቸው አሜሪካውያን ተማሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመውሰድ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶችን፣ ታሪካዊ ቦታዎችን እና አኗኗሮችን እንዲጎበኙ አድርጋለች። ከነዚህ ቦታዎች ደግሞ የትምህርት ማዕከል የከፈተችበት ኩታበር አንዱ ነው።

"በአሜሪካ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ተዛብቶ የሚሰሙትን አፍሪካዊ መሆን ምን ማለት ነው፣ አፍሪካ ውስጥ የሚኖሩ አፍሪካውያን ለዓለም ታሪክ፣ ሥነ-ጽሁፍ፣ ሂሳብ፣ ሳይንስ እና ህክምና ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል የሚሉትን መረጃ ማስተካከል ችለናል። ባዩትና በሰሙት ውስጥ ያሳዩትን እድገት እንዲሁም እራሳቸውን የሚያዩበት መንገድ እንዴት እንደተቀየረ ማየት ችለናል።"

የሊያ እናት ወይዘሮ አምሳለ አበጋዝ ከእናትነት ባሻገር ሊያን በፋውንዴሽኑ ውስጥ ያግዟታል። ወይዘሮ አምሳለ ልጃቸው በትውልድ ቦታቸው የጀመረችው በጎ ሥራ በተለይ ለሴቶች ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት እድል እንዲፈጥር ይመኛሉ።

ሊያ አሁን በትምህርት ሳይኮሎጂ የዶክትሬት ዲግሪዋን ለመጨረስ አንድ ዓመት ቀርቷታል። ያንን ስታጠናቅቅ ቀጣይ እቅዷ የተማሪዎች የልምድ ለውውጥ ፕሮግራሙን ከማጠናከር በተጨማሪ በኩታበር ለሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት መክፈት ይሆናል።

XS
SM
MD
LG