በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከህወሀት ጋር ድርድር ሊጀመር የሚችልበት ዕድል መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠቆሙ


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥት ከህወሓት ጋር ሊደራደር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት እና ህወሓት እየተደራደሩ እንደሚገኙ የሚወሩ ጭምጭምታዎች ሐሰት መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ አካላት መካከል ድርድር እየተደረገ እንደሆን፣ የምክር ቤቱ አባል የሆኑት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ላነሱላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “እስካሁን፣ እስከዚህች ደቂቃ ድረስ የተደረገ ድርድር የለም” ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልልን በማስተዳደር ላይ የሚገኙት ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረ ሚካዔል በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ፣ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በተለያየ መልኩ ድርድሮች እየተደረጉ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልል ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው በቅርቡ የተመለሱት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ የጦርነቱ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያዊ መፍትሄ ለማምጣት ተነሳሽነት እናዳላቸው እንዳሳወቋቸው ገልፀዋል።

ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ግጭቶች መቀነሳቸውንና ለሰላምም የተሻለ ዕድል እንዳለ ገልፀው ብሔራዊ ምክክሩን ለመጀመርና የሰላሙን መንገድ ለማፈላለግ ግጭቶች መቆም እንደሚገባቸው መጠቆማቸው አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬው ማብራሪያቸው፣ እርሳቸውም ለድርድር ብዙ እንደሚወራ መስማታቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን እስካሁን ድርድር አለመደረጉን አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ማለት ግን “እስከናካቴው ድርድር አናደርግም ማለት አይደለም” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለማጽናት ድርድር የተሻለው አማራጭ ከሆነ ተግባራዊ እንደሚደረግ በጠቆሙበት ንግግራቸው፣ “ኢትዮጵያን ለማጽናት ህይወታችንን እና ገንዘባችን የምንገብር ከሆነ፣ ኢትዮጵያን ለማጽናት ስሜቶቻችን አምቀን መነጋገር የሚቻል ከሆነ በደስታ ማየት ነው” ብለዋል፡፡

ድርድር ማለት እርቅ እንዳልሆነም የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግስታቸው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ምንም እንደማይደራደር ከዚህ በፊት አቋም መያዙን እና አሁንም የሚደረግ ድርድር ከዚህ አቋም ውጭ እንደማይሆንም ነው ያብራሩት፡፡ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉም፣ በድርድር የሰላም አማራጭ ካለ፣ “ህወሓት ቀልብ ከገዛ፣ በጦርነት እንደማያዋጣው እና እንደማያሸንፍ ከተገነዘበ፣ እኛ በደስታ ነው የምናየው” በማለት መንግስታቸው ለድርድር ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከህወሓት ጋር ለመደራደር ዝግጁ ስለመሆናቸው”፣ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መናገራቸውን በተመለከተ አሶሼትድ ፕሬስ በቅርቡ ቢዘግብም፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፣ እስካሁን ”በአሸባሪነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር እንደራደራለን የተባለ ነገር የለም” ማለታቸው ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬው የምክር ቤቱ ሦስተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ቆይታቸው ስለ ሀገራዊ ምክክሩም ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣

“እኔ ድርድር ብዬ የማስበው ትናንት በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውን አካታች ብሔራዊ ምክክር ነው” ብለዋል፡፡ በሀገራዊ ምክክሩ፣ በተለያዩ የማያግባቡ ጉዳዮች ላይ ጥልቀት ያለው ውይይት እና ክርክር እንደሚደረግ ገልጸው፣ መግባበት ካልተቻለ ግን በሕዝበ ውሳኔ መፍትሔ እንደሚያገኝ ነው የጠቆሙት፡፡ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አባላት ከተለያዩ አካባቢዎች እና ከተለያየ ዕምነት ተከታዮች የተመረጡ መሆናቸውንም አድንቀዋል፡፡

የህወሓት አንጋፋ አመራሮችን ከእስር መለቀቅ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ፣ እስረኞቹ የተፈቱት በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እነዚህም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት፣ ጤንነታቸውን ጨምሮ የታሳሪዎችን ሁለንተናዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም ”ያገኘነውን ድል ለማጽናት” ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት፡፡ የክስ ማቋረጥ ሂደቱ የተከናወነው ሕግን በተከተለ መልኩ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በእስረኞቹ መፈታት ኢትዮጵያ በርካታ ጥቅሞችን ማግኘቷን ቢገልጹም፣ ስለጥቅሞቹ በዝርዝር ከማስረዳት ግን ተቆጥበዋል፡፡

ህወሓት በአፋር በኩል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአዲስ መልክ ከፈተ የተባለውን ውጊያ በተመለከተ በሰጡት ገለጻ ደግሞ፣ የህወሓት ዓላማ የእርዳታ ምግብ ወደ ትግራይ እንዳይደርስ ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱን ሲያስረዱ፣ የዓለም መንግስታት ከትግራይ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚከሱበት ጉዳይ ሁሉ አልቆ በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ችግር ምክንያት ሰዎች በርሃብ እየሞቱ ነው የሚል ክስ ብቻ መቅረቱን በመጥቀስ፣ የህወሓት ዓላማ ይህ ክስ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡ ሕወሓት ጦርነቱን የከፈተው፣ የዕርዳታ ምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን የጫኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የጭነት መኪኖች ከሰመራ ተነስተው ወደ መቀሌ ጉዞ በጀመሩበት ዕለት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክንያታቸው በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

ህወሓት በበኩሉ የትግራይ ውጭ ጉዳዮች በተባለ ቢሮው አማካኝነት ጦርነቱን የከፈተበትን ምክንያት ሲያስረዳ፣ የአፋር ልዩ ኃይል እና በቀጥታ በኤርትራ መንግሥት የሚመራ ያለው የቀይ ባህር አፋር ኃይል በትግራይ ክልል ላይ የደቀኑትን ስጋት ለመከላከል እንደሆነ መግለጹ አይዘነጋም፡፡ የአፋር ክልል መንግሥት አመራሮች እና የቀይ ባህር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አመራሮች ግን ይህን ውንጀላ እንደማይቀበሉት ሰሞኑን ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡

በአፋር ክልል ዞን ሁለት ያለው ውጊያ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲስተጓጎል ምክንያት አይሆንም ያለው ሕወሓት፣ እርዳታው እንዳይደርስ እያደረገ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን በመግለጽ ይከሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ታዲያ በዛሬው ማብራሪያቸው፣ ሕወሓት ሆን ብሎ ከሰመራ - መቀሌ ያለውን የእርዳታ መስመር፣ ሆን ብሎ ጦርነት በመክፈት ለፖለቲካ ፍጆታ ሲል እንደዘጋው ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ በነበረችበት ባለፉት 6 ወራት ኢኮኖሚያዊ እድገት መቀጠሉንም ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የዋጋ ንረት ግን ከፍተኛ ፈተና መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ ይህም በዋናነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የዋጋ ንረት ጋር ግንኙነት እንዳለውም አብራርተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG