በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል


ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል
ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል

ከ2003 ዓ.ም መጋቢት ጀምሮ ላለፉት 11 ዓመታት በዓባይ ወንዝ ላይ ሲገነባ የቆየው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ካሉት 13 የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች መካከል አንዱ ዛሬ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ታውቋል፡፡ ኃይል ማመንጨት የጀመረው 10ኛው ተርባይን (ዩኒት) ሲሆን፣ የሚያመነጨው የኃይል መጠንም 375 ሜጋ ዋት እንደሆነ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከ11 ዓመታት በፊት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም አሁን በሕይወት በሌሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥለት፣ በ80 ቢሊዮን ብር ወጪ በስድስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ታቅዶ የነበረው ግድቡ እስካሁንም ድረስ መጠናቀቅ አልቻለም፡፡ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የግድቡ የግንባታ መጠን 83.9 በመቶ መድረሱና ለዚህም ከ 163 ቢሊዮን ብር በላይ እንደወጣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

የግድቡ የግንባታ ጊዜ መራዘም ፣ ውስጣዊ እና ውጫዊ ቀውሶችን አስከትሏል፤ የነበሩትም እንዲባባሱ አድርጓል፡፡የግንባታ ጊዜው መራዘም ከውስጣዊ የኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖው ባለፈ፣ ግማሽ የሚሆኑ ዜጎቿ የኤሌክትሪክ ኃይል በማያገኙባት ኢትዮጵያ ማህበራዊ ቀውሶችም እንዳይሻሻሉ ማድረጉ ይነገራል፡፡ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ያለው ተጽዕኖም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ዲንጋይ በተጣለበት ልክ በሰባተኛው ዓመት፣ በኢትዮጵያ መንግስታዊ የሥርዓት ለውጥ ተከስቶ ወደ መሪነት የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ለግድቡ ግንባታ መጓተት፣ ለጥራት ጉድለት እና ለወጪው መብዛት ህወሃትን “ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ” ማድረጋቸው እና የግንባታው ሂደትም እንዲቀየር ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሀገር በቀሉ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ በግድቡ ግንባታ ላይ ያለው ተሳትፎ እንዲቋረጥ ተደርጎ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ለውጭ ኩባንያዎች እንዲሰጥ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሚቀርብበትን ክስ የማይቀበለው ህወሃት፣ ይልቁንም በጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አስተዳደር “ግድቡ ተሽጧል” እስከማለት ከሷል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል
ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት 11 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን ውዝግብ ዛሬም እልባት አላገኘም፡፡ ይልቁንም እየተባባሰ ሄዷል፡፡የሦስቱ ሀገራት ውዝግብ ይበልጥ እየተካረረ የሄደው ደግሞ፣ ኢትዮጵያ በሐምሌ 2012 ዓ.ም የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት ማከናወኗን ይፋ ካደረገች በኋላ ነው፡፡ ሁለተኛው ሙሌት ደግሞ በቀጣዩ ዓመት ነሐሴ ወር ላይ መከናወኑ ይታወቃል፡፡

ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ስጋቶች እንዳሉባቸው የሚገልጹት ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት (ግብጽ እና ሱዳን)፣ ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት እና በየዓመቱ ከግድቡ የምትለቀውን የውሃ መጠን በተመለከተ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ አስገዳጅ ስምምነት ላይ የመድረስ ፍላጎት እንደሌለለት እና ፈጽሞ እንደማትቀበልም አቋም ይዛለች፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል
ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል

የሦስቱ ሀገራት ውዝግብ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ እስከመሆንም የደረሰ ሲሆን፣ ባለፈው መስከረም ወር ላይ በጉዳዩ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ፣ ሦስቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት መሪነት የተጀመረውን የድርድር ሂደት እንዲያስቀጥሉ እና ምክንያታዊ በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡

እስካሁን የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት የተሳነው በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚደረገው ድርድር ለመጨረሻ ጊዜ ከተካሔደ ከ10 ወራት በላይ ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ ለድርድሩ አለመቀጠል ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ ታራምዳለች የሚሉትን “ግትር አቋም” በምክንያትነት ሲያቀርቡ፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ “ግትር አቋም” የሚያራምዱት ሁለቱ ሀገራት እንደሆኑ በመግለጽ ትከሳለች፡፡ያም ሆነ ይህ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ከሕዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጨት ጀምራለች፡፡ “ግንድ ይዞ ይዞራል” የተባለለት ዓባይም ታሪኩን ማደስ ጀምሯል፡፡

ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 5,150 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ግድቡ፣ በአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ ግድብ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኘው ግድቡ 145 ሜትር ከፍታ እና 1,780 ሜትር ርዝማኔ ሲኖረው፣ ውሃው ከግድቡ ወደ ኋላ 240 ኪሎ ሜትር ድረስ እንደሚያርፍ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

XS
SM
MD
LG