የመድሃኒት ቁሳቁሶችን የጫኑ ሁለት አውሮፕላኖች ትላንት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ወደምትገኘው የትግራይ ክልል መላኩን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
ከሐምሌ ወዲህ ወደ ትግራይ የተላከ የመጀመሪያው የህክምና አቅርቦት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን አቅርቦቱ እንደ የወባ በሽታ መከላከያ፣ ባክቴሪያ ማጥፊያ እና የስኳር በሽታ መድሃኒቶች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል። ለረጅም ግዜ ስትይታከሙ የቆዩ ከፍተኛ የምግብ እጥረት በሽታ እና ህመሞችን ለማከም የሚረዱ ማከሚያ መሳሪያዎችም ቁሳቁሶቹ ውስጥ ተካተዋል።
"ይህ ጥሩ ዜና ነው ያሉት" የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ክሪስቲያን ሊንድሜየር፣ የህክምና ቁሳቁሶቹን እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው ሰዎች ለማድረስ ነዳጅ አለመኖሩ ግን አሁንም ችግር ሆኖ እንደቀጠለ ተናግረዋል።
"ከጥር 24 እስከ 29 በተካሄደው የክትባት ዘመቻ ክትባቶቹን የያዙትን ቀዝቃዛ ሳጥኖች ለመጓጓዝ እንስሳቶችን ተጠቅመናል። ይሄ ግን ዘላቂ የትራንስፖርት አገልግሎት አይደለም። ስለዚህ ቁሳቁሶቹን ወደየጤና ተቋማቱ ለማድረስ የነዳጅ እጥረቱ ጉዳይ በሀገር ውስጥ ባለስልጣናትና በ ዓለም አቀፍ አግሮች በኩል እንደሚፈታ ተስፋ እናደርጋለን።"
የዓለም ጤና ድርጅት 300 ቶን የሚመዝን የህክምና ቁሳቁሶች እና 33.5 ቶን የሚመዝን የመድሃኒት አቅርቦቶች ለመጓጓዝ እየጠበቁ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ለዚህ 200 ሺህ ሊትር የሚሆን ነዳጅ በየሳምንቱ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግልጿል።