በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያን ችግር በውጪ ጣልቃ ገብነት መፍታት እንደማይቻል የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደሮች አሳሰቡ


የኢትዮጵያን ችግር በውጪ ጣልቃ ገብነት መፍታት እንደማይቻል የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደሮች አሳሰቡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:41 0:00

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ችግር በውጪ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ሊፈታ እንደማይችል እና መፍትሄው ከውስጥ መምጣት እንዳለበት የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ አምባሳደሮች አምባሳደር ቲቦር ናዥ እና አምባሳደር ዶናልድ ቡት ተናግረዋል። አምባሳደሮቹ የዘር መከፋፈል ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር እንደዳረጋት ገልፀው ኢትዮጵያኖች ልዩነታቸውን አቻችለው በአንድነትና በሰላም መኖር የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያና በጊኒ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትና በትራምፕ አስተዳደር ረዳት የውጭ ጉዳይ የነበሩት ቲቦር ናዥ እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ ላይቤሪያ እና ዛምቢያ አምባሳደር የነበሩት ዶናልድ ቡት ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ ድምፅ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያውያን ለውጪ ሀይል ግፊት የማይንበረከኩ መሆናቸውን ማስተዋላቸውንና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሚና ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፈሪ ፌልትማን እና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጆ ኦባሳንጆ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ቀውስ እንድትወጣ እያደርጉት ያሉትን ጥረት ያደነቁት አምባሳደር ቡት፣ ኢትዮጵያውያን ግን ለውጪ ግፊት በቀላሉ እጅ አይሰጡም ብለዋል።

በዚህ የሚስማሙት አምባሳደር ናዥ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር የምትወጣው መፍትሄው ከራሳቸው ከኢትዮጵያውያን ሲመጣ ብቻ መሆኑን አስምረውበታል።

ናዥ አክለው የምዕራብ ሀገራት ብቻ የኢትዮጵያን ችግር ለመቅረፍ መቀናጀታቸው በቂ አለመሆኑንና ቻይና እና መካከለኛው ምስራቅ ያሉ ሀገራትም የመፍትሄው አካል መሆን አለባቸው ሲሉ ሀሳባቸውን ስጥተዋል።

ሁለቱም የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች ከአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ካሮል ካስቲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሲተገበር የኖረው ዘርን መሰረት ያደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት ኢትዮጵያን አሁን ላለችበት ችግር መሰረት እንደሆነም ጠቅሰዋል። የደርግን መውደቅ ተከትሎ ስልጣን የያዘው የህወሃት መንግስት ይህን ስርዓት ማምጣቱን ያስታወሱት ናዥ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን አለመስራቱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ችግር የተባባሰው የፖለቲካ አመራሮች ከህዝቡ ድጋፍ ለማግኘት ዘርን መጠቀማቸው ነው ያሉት አምባሳደር ቡት በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተሞከረው ዘርን መሰረት ያደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት የታሰበውን ውጤት አለማምጣት ለዚህ ልዩነት መስፋፋት አስተዋፅኦ እንዳደረገ አስምረውበታል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ አድርገዋቸው የነበሩ የፖለቲካ መሻሻሎች በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ቦታ የሚሰጣቸው ነበሩ ያሉት አምባሳደር ናዥ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እንድትገባ መፍቀዱን በጥብቅ ተቃውመዋል።

አምባሳደር ናዥም የኢትዮጵያ መንግስት የፈፀመው ዋነኛ ስህተት ህወሃት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ላደረሰው ጥቃት ምላሽ ሲሰጥ ኤርትራ ጣልቃ እንድትገባ መፍቀዱ ነው ሲሉ የኤርትራን ሚና አውግዘዋል።

በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ላለው ግጭት እያበረከቱት ያለው አፍራሽ እና ገንቢ ሚና የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ያለው ችግር ከስር መሰረቱ እንዲፈታ ከተፈለገ ኢትዮጵያኖች አንድ ላይ ተቀምጠው ስለወደፊታቸው መነጋገር አለባቸው ብለዋል። ከኢትዮጵያ ውጪ ያለው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለኢትዮጵያ መሆን አለበት ብለው የሚያስቡትን አቅጣጫ ከማዘጋጀት ይልቅ፣ ህዝቡ በራሱ ችግሮቹን መፍታት የሚችልበትን መንገድ በማቸቻቸት ብቻ እንዲያግዝ አሳስበዋል።

XS
SM
MD
LG