ኤርትራ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ዓርብ በኢትዮጵያ ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ በኤርትራ ጦር፣ በገዥው ፓርቲ አባላትና በሁለት ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ላይ የጣለቸው አዲስ ማዕቀብ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምትከተለው የተሳሳተና የጠበኝነትና ፖሊሲ ቀጣይ እምርጃ ስትል እንደምትቃወመው አስታወቀች፡፡
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ የህገ ወጡና ሞራል አልባው ማዕቀብ ዋና ዐላማ፣ የኤርትራን ህዝብ መከራ ለማብዛትና የአፍሪካን ቀን እንዳይረጋጋ ለማድረግ የወጣ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የፌደራል ግምጃ ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ ወታደሮቹ በሰሜኑ ጦርነት ከኢትዮጵያ ጋር ሆነው ተሳተፈዋል በተባለው በኤርትራ የመከላከያ ኃይል፣ በብቸኛው የኤርትራ ገዥ ፖለቲካ ፓርቲ በሆነው ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ላይ ማእቀብ መጣሉን አስታውቋል፡፡
እንዲሁም ከግለሰቦች የኢኮኖሚ አማካሪውን ሀጎስ ገ/ህይወት ወ/ኪዳን፣ የኤርትራ ደህንነት ሹም አብራኻ ካሳ ነማሪያም እና በንግድ ዘርፍ ከህድሪ ትረስትና የቀይ ባህር ኮርፖሬሽን ከሚሰሩት ሁለት ግለሰቦች ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ውስጥ ይገኙበታል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትናንት ባወጡት መግለጫ የኤርትራ ኃይሎች በኢትዮጵያ መገኘት ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ በማድረግና ግጭቱንም በማራዘም ትልቅ መሰናክል ይፈጥራል ማለታቸው ይታወሳል፡፡