በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአየር ንብረት ለውጥ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ በሰውና እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው


የአየር ንብረት ለውጥ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ በሰውና እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:03 0:00

የአየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ ሀብት መመናመን በኢትዮጵያ የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ባስከተለው ከፍተኛ የዝናብ እጥረትና የአካባቢ ሙቀት መጨመር ምክንያት ምርት በመቀነሱ የምግብ ተረጂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑንና በድርቅ ምክንያት ምስራቅ ሸዋ በሚገኘው አዳሚ ቱሉ ወረዳ ብቻ በአንድ አመት ውስጥ ከ ዘጠኝ ሺህ በላይ ከብቶች መሞታቸውን ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ በመባል የሚታወቀው ጥምረት አስታውቋል።


የ68 አመቱ አቶ ኒኔ ሆርሲሳ በምስራቅ ሸዋ፣ አዳሚ ቱሉ ወረዳ ተወልደው ያደጉ ገበሬ ናቸው። በልጅነታቸው የነበረውን አካባቢ ሲያስትውሱም በጥቅጥቅ ደን የተሸፈነና ልዩ የተፈጥሮ ውበት የተላበሰ ከመሆኑ በላይ ዝናብ እንደልብ ይጥል ነበር ይላሉ።

ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ኒኔ ያ በልጅነታቸው በደን ተሸፍኖ የሚያውቁት መንደራቸው ተራቁቶ ወደ በረሃማነት መቀየሩ ያሳዝናቸዋል። በተለይ ደግሞ ዝናብ እንደልብ ባለመጣሉ በቆሎ በቀላሉ እንዳይዘሩ ስላደረጋቸው ቤተሰባቸው ስጋት ላይ መውደቁን ያስረዳሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለው የዝናብ መቀነስና የአካባቢ ሙቀት መጨመር አቶ ኒኔ የሚኖሩበት አዳሚ ቱሉ ወረዳን ጨምሮ ምዕራብ አርሲን፣ እንዲሁም የአዋሳን ዙሪያ የሚያካትተው መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያደረሰ ነው።

በተለይ የዝናብ መቀነስ ዋና የአካባቢው የሰብል ምርት የሆነው በቆሎ እንደልብ እንዳይበቅል በማድረጉ ማህበረሰቡ በአጭር ግዜ የሚደርሱና አነስተኛ ምርት ያላቸውን እህሎችን እንዲዘራ እየተገደደ መሆኑን የኢትዮጵያ ስነ-ህዝብ፣ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ወይም በምፅህረ ቃሉ ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ በመባል የሚታወቀው ጥምረት የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አበባየሁ ካሳዬ ነግረውናል።

ከምርት መቀነስ በተጨማሪ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ከዚህ በፊት ታይተው የማያውቁ የአዝዕርት በሽታዎች መብዛታቸውም ገበሬውን ለከፍተኛ ችግር እንደዳረገው አቶ አበባየሁ ያስረዳሉ።

አቶ ኒኔ እንደሚሉት ለፀረ ተዋስያን ከሚወጣው ወጪ በተጨማሪ የአፈር መሸርሸር ከግዜ ወደግዜ መሬቱን ለምነት በማሳጣቱ ገበሬው ማዳበሪያ ለመጠቀም ተገዷል።

የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው የዝናብ እጥረት ምክንያት በአዳሚ ቱሉ ወርዳ ብቻ በ2013 ዓ.ም በ3700 ሄክታር መሬት ላይ ተዘርቶ የነበረ እህል ሳይበቅል ቀርቷል፣ ከ13 ሺህ 800 ሄክታር በላይ የሚሆን መሬትም ሳይዘራበት ቀርቷል። በዚህ ምክንያት በአካባቢው ድርቅ እየተባባሰ ሄዶ በአንድ አመት ውስጥ 9 ሺህ 46 ከብቶች ሞተዋል። ከአመት በፊት በ 7 ቀብሌዎች ውስጥ ይረዱ የነበሩ 13ሺህ 590 ሰዎች ቁጥርም ወደ 20 ቀበሌዎች አድጎ አሁን 54 ሺህ10 ሰዎች እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። አቶ ኒኔም በኖሩበት ሀገር ከብቶች የሚበሉት አጥተው ሲሞቱ ማየት እጅግ ያሳዝናቸዋል።

የአየር ንብረት ለውጡ ያስከተለው የምርት ማነስ ከሌሎች ሀገራዊ ሁኔትዎች ጋር ተደማምሮ በአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ ያደረሰውን የዋጋ ግሽበትም አቶ አበባየሁ እንዲህ ይገልፁታል።

የዝዋይ፣ ላንጋኖ፣ አብያታና ሻላ ሀይቆችን እንዲሁም በርዳታ የዱር እንስሳና እፅዋትን ጨምሮ ከፍተኛ የብዝሃ ህይወት ክምችት ባለበት መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ የህዝብ ብዛት ቁጥር መጨመርና ያንን ተከትሎ በሚመጡ የእርሻ መስፋፋቶች ምክንያት እየተራቆተ መሄዱ ለአየር ንብረት ለውጡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ቢያደርግም፣ አቶ አበባየሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ የካርበንዳዮክሳይድ ልቀት እያስከተለ ያለው የአካባቢ ሙቀት መጨመርም የራሱ አስተዋፅኦ አለው ይላሉ።

አቶ አበባየው የአየር ንብረት ለውጥ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆም ሆነ በቀሪው የኢትዮጵያ አካባቢዎች እያደረሰ ያለውን ተፅእኖ ለመከላከል ለአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ያሰምሩበታል። የቀሩ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅና የተራቆቱትን መልሶ ለማልማትም መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ማህበረሰቡ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም መክረዋል።
XS
SM
MD
LG