በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የህፃናትን ስነ-ባህሪና እድገት የሚያጠናው የመጀመሪያው ተቋም


የህፃናትን ስነ-ባህሪና እድገት የሚያጠናው የመጀመሪያው ተቋም
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:21 0:00

ጎጆ የህሙማን መጠለያ ተቋምን በመመስረት በሺዎች ለሚቆጠሩ አቅመ ደካማ ህሙማን ድጋፍ እየሰጠች የምትገኘው ዶክተር ሰላሜነሽ ፅጌ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የህፃናት ስነ-ባህሪና የእድገት ሁኔታን የሚያጠና ተቋም በጥቁር አምበሳ ሆስፒታል ስር እንዲጀመር ያደረገች የህፃናት ሀኪም ናት።

ዶክተር ሰላሜነሽ የህፃናት ህክምና ትምህርቷን ለመጨረስ የመጨረሻ አመት የልምምድ ስራዋን በምትሰራበት ወቅት ነው ዴቨሎፕመንታል ፔዲያትሪክስ ከተሰኘው የህፃናትን ስነ-ባህሪና የእድገት ሁኔታን የሚያጠና የህክምናት አይነት ጋር የተዋወቀችው።

ለህፃናት መሰረታዊ የሆነው ይህ የህክምና አገልግሎት ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲም ትምህርቱ አይሰጥም። ይህ ዶክተር ሰላሜነሽን ስለህክምናው የበለጠ እንድታነብ፣ እንድታጠናና የመመረቂያ ስራዋን በዚሁ የህክምና አይነት ላይ እንድታተኩር አደረጋት። ከሁለት አመት በፊት ትምህርቷን አጠናቃ ስትመረቅም በጥቁር አምበሳ ሆስፒታል የመጀመሪያውን ዴቨሎፕመንታል ክሊኒክ እንዲጀመር አደረገች።

በህፃናት ባህሪና እድገት ዙሪያ የሚሰጠው አትኩሮት በፖሊሲ ደረጃ ድጋፍ እንዲያገኝ ለማድረግና የህክምና አገልግሎቱን በሀገር ደረጃ ለማሳደግ ዋንኛ መሳሪያው እውቀትን ማሳደግ ነው ብላ የምታምነው ዶክተር ሰላሜነሽ በአሁኑ ሰዓት በካናዳ፣ ቶሮንቶ ዩንቨርስቲ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች።

ይህን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የህክምና አገልግሎትና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መጥተው ማረፊያ በማጣት ለብዙ ችግር ይጋለጡ ለነበሩ የተለያዩ ህሙማን ማረፊይ የሆነውን ጎጆ የህሙማን መጠለያ ተቋምን የመሰረተችው ዶክተር ሰላሜነሽ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየአመቱ በሚያዘጋጀው የወጣት አፍሪካዊ መሪዎች የልምድ መለዋወጫ መድረክ ላይም ዘንድሮ ኢትዮጵያን ወክላ እንድትሳተፍ መርጧታል።

ዶክተር ሰላሜነሽ በ2007 ዓ.ም ነው የመጀመሪያ ዲግሪ የህክምና ትምህርቷን ያጠናቀቀችው። በአመቱ ደግሞ ሶስት አመት የፈጀውን የህፃናት ህክምና ትምህርት ለመማር ወደ ትምህርት ቤት ተመለሰች። ከትምርህት ቤት ውጪ በህክምና ስራው ላይ ያሳለፈቻቸው ሁለት አመታት አጭር ግዜ ቢመስሉም ገዝፈው የሚታዩና በበርካቶች ህይወት ላይ ለውጥ ማምጣት የቻሉ ስራዎችን መስራት የቻለችው ዶክተር ሰላሜነሽ ወደ ህክምና ሙያ እንዴት እንደተቀላቀለች ነግራናለች።

ህክምና ትምህርት ቤት ከገባች በኃላ የነበረባት የቆዳ ህመም በቀላሉ የሚድንና መድሃኒቱም የሚታወቅ መሆኑን የተረዳችው ዶክተር ሰላሜነሽ ፣ እሷ ለውጥ ልታመጣበት የምትችለው የተሻለ የህክምና አይነት መፈለግ ጀመረች።

በርካቶች ለሰዎች መልካም ማድረግን ይፈልጋሉ፣ ያስባሉ። ወደ ተግባር የሚቀይሩት ግን ጥቂቶች ናቸው። ዶክተር ሰላሜነሽ በወጣትነት እድሜዋ ለሰዎች የማሰብ መልካምነንትንና፣ የጀመሩትን ከግብ የማድረስ ፅናትን ከየት ተማረችው?

ታዲያ በርካታ በሷ እድሜ ያሉ ወጣቶች ከዶክተር ሰላሜነሽ ምን ይማራሉ? የመጨረሻ ያቀረብኩላት ጥያቄ ነው።

ዶክተር ሰላሜነሽ በቀጣይ ማሳካት የምትፈልጋቸው ሁለት ትልልቅ ህልሞች አሏት። ጎጆ የህሙማን መጠለያን አሳድጎ ትልቅ ማድረግና ገና ያልተደረሰላቸውን ህሙማንን ማገዝ እንዲችል ማድረግ አንዱ ሲሆን ሁለተኛው ዲቨሎፕመንታል ፔዲያትሪክስ ህክምናን በኢትዮጵያ በማሳደግ የህፃናት ማገገሚያ ማዕከል ማቋቋም ነው።

XS
SM
MD
LG