(ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ)
ከሰባት አመት በፊት በጥቁር አምበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የመጨረሻ አመት የህክምና ትምህርትቷን ትከታተል የነበረች አንዲት ወጣት በየቀኑ በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ላስቲክ አንጥፈው የሚተኙትን፣ ወይም የሚበሉት አጥተው የሚለምኑትን ህመምተኞች ስታይ በየቀኑ ልቧ ይሰበር ነበር።
ይህች ወጣት - ዶክተር ሰላሜነሽ ፅጌ ትባላለች። የ29 አመት ወጣት ስትሆን አሁን በጥቁር አምበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስትና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የህፃናት ህክምና ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር፣ እንዲሁም ለነዚህ ማረፊያ ያጡ ህሙማን የክፉ ቀን ደራሽ የሆነው 'ጎጆ ህሙማን ማረፊያ' መስራችና ፕሬዝዳንት ናት።
ዶክተር ሰላሜነሽ የህክምናት ትምህርቷን ለመጨረስ የልምምድ ስራ እየሰራች በነበረበት ወቅት ያጋጠማት ታካሚ ነው ልቧን ለሚሰብረው ችግር እልባት ለመስጠት ምክንያት የሆናት።
ይህ አጋጣሚ ለጎጆ ህሙማን ማረፊያ መመስረት ምክንያት ሆነ። ጓደኞቿን በማሰባሰብ ስራውን የጀመረቸው ለምግብ፣ ለመጠለያ፣ ለትራንስፖርት ገንዘብ በማጣት መሬት ላይ ወድቀው የሚገኙ ህሙማን ምን ያክል ናቸው የሚለውን በማጥናት ሲሆን በወቅቱ በጥቁር አምበሳ ብቻ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መጥተው ህክምናቸው ቶሎ ባለማለቁ ለልመና የተዳረጉ 70 ሰዎችን አገኙ። ከተለያዩ የመንግስት ሪፈራል ሆስፒታሎች የተገኙት ሲደመሩ ግን እስከ 300 ይደርሳሉ።
ጎጆ የህሙማን ማረፊያ በ2007 ዓ.ም ተቋም ሆኖ ለመመስረት ፈቃድ ሲያወጣ የመጀመሪያ ስራው ዶክተር ሰላሜነሽና ጓደኞቿ ከኪሳቸው በሚያዋጡት ገንዘብ ለህሙማኑ ምግብ ማቅረብ ነበር።
በወር አንዴ የነበረው ይህ የመመገብ ሂደት አድጎ ዛሬ ተክለሀይማኖት ጤና ጣቢያ ግቢ ውስጥ የሚገኘውን መጠለያ ለመክፈት ችሏል። ህንፃውን ለመገንባት የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና ቃሊቲ ኮንስትራክሽን ዕቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮና የጤና ሚኒስቴርም ድጋፍ አድርገዋል። መጠለያው ተሰርቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሶስት አመት የሆነው ሲሆን 52 ህሙማንን ከነአስታማሚዎቻቸው የማስጠለል አቅም አለው። እስካሁንም የምግብ አገልግሎት የሚያገኙትን ሳይጨምር ከ81 ሺህ በላይ ሰዎች በመጠለያው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ለመሆኑ እነዚህ ህመምተኞች ከየት አካባቢ ነው የሚመጡት?
ዘጠና ከመቶ የሚሆኑት በጎጆ ውስጥ አገልግሎት የሚያገኙት ህሙማን የካንሰር ተጠቂዎች ናቸው። ይህ የሆነው ለምንድ ነው ስንል ዶክተር ሰላሜነሽን ጠየኳት።
ዶክተር ሰላሜነሽ ከበጎ ስራዋ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የሌለና የህፃናት ስነ-ባህሪና የእድገት ሁኔታን የሚያጠና ዴቨሎፕመንታል ፔዲያትሪክስ የተሰኘ የህክምና አይነት በጥቁር አምበሳ ሆስፒታል መስርታለች። በነዚህ ሁለት ስራዎቿ ምክንያትም በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት በየአመቱ ለወጣት የአፍሪካ አመራሮች የልምድ መለዋወጫ መድረክ እንዲሆን በሚዘጋጀው የማንዴላ ፌሎሺፕ ተሳታፊ ስትሆን በተመሳሳይ ሰዓት እንዲሁ በካናዳ የዴቨሎፕመንታል ፔዲያትሪክስ ትምህርት እንድትከታተል ባገኘችው እድል እየተማረች ትገኛለች።
አድማጮች በነዚህና ዶክተር ሰላሜነሽ በተለይ በህፃናት ህክምና ዙሪያ እየሰራች ስላለቻቸው ፈር ቀዳጅ ስራዎች የሚቃኝ ዝግጅት ይዘን እንመለሳለን።