በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአይምሮ ጤና ከአካላዊ ጤና እኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል


የአይምሮ ጤና ከአካላዊ ጤና እኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:28 0:00

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት የአይምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። በሽታው በቀጥታ በአይምሮጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ወረርሽኙ በሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ባደረሰው ተፅእኖ ምክንያት ለአይምሮ ጤና ይደረግ የነበረው የገንዘብ ድጎማ በመመናመኑም ቀድሞውንም ደካማ የነበረው የህክምና አቅርቦት መቀነስ ችግሩን እያባባሰው ነው።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ መሰራጨቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ በሽታውን ለመቆጣጠር የተወሰዱት እንደ - የአካል ርቀትን መጠበቅ፣ ከቤት ያለመውጣት፣ የስፖርትና መዝናኛ ቦታዎች መዘጋት፣ ከቤት መስራት እና ከሀገር መውጣት አለመቻል የመሳሰሉት ክልከላዎች- ብዙዎችን ለከፋ ጭንቀት፣ የአይምሮ መረበሽ እና ስጋት አጋልጧል። በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙ ሰዎችም በሽታው ጥሎት የሚሄድ የአይምሮ ጤና እክሎች ተጋላጭ እንደሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ይህ ጫና በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስል በቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ የአይምሮ ሀካሚ እና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትን ዶክተር ሙሉቀን ተስፋዬን ጠይቀናቸዋል።

ኮቪድ 19 በአይምሮ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ የሚጀምረው በሽታው ይዞኝ ይሆን ከሚል የእለት ተእለት ጭንቀት ነው። ይህ ጭንቀት እየከፋ ሲሄድ ታዲያ አይምሮን ሊያውክና ሰዎች የዘወትር ተግባራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ ሊያግዳቸው እንደሚችል የነገሩን ደግሞ ለ14 አመታት በአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉትና አሁን በግል ድርጅት የህፃናት ጉዳይ ላይ የሚሰሩት የአይምሮ ሀኪም ዶክተር ሚኒሊክ ደስታ ናቸው።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት አብሮ መኖርን እንደ ባህል አርጎ ለሚኖር ህብረተሰብ፣ ወረርሽኙ ያስከተላቸው ክልከላዎች በራሳቸው አስጨናቂ ናቸው። በዛ ላይ ደግሞ አብዛኛው ህዝብ መደበኛ ባልሆነ የኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ በተሰማራበት ታዳጊ ሀገር ላይ፣ የእለት ገቢን የሚያስተጓጉል ወረርሽኝ ሲጨመርበት የአይምሮ ጤና መታወከ ሊያስከትል እንደሚችል ዶክተር ሚኒሊክ ይገልፃሉ።

ያም ብቻ አይደለም ያላሉ ዶከተር ሚኒሊክ። በበሽታው ዙሪያ የሚሰራጩ እውነተኛና ሀሰተኛ መረጃዎች መብዛታቸውም ሌላ የጭንቀት ምንጭ ናቸው።

ጤና ማለት አካላዊ ብቻ ሳይሆን የአይምሮም ጤና ነው። ሆኖም በኢትዮጵያም ሆነ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ለአይምሮ ጤና የሚሰጠው ቦታ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ለበሽታው የሚሰጠው ህክምና ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፊትም በጣም ውስን እንደነበር የሚገልፁት ዶክተር ሚኒሊክ ኢትዮጵያ ውስጥ የአይምሮ ጤና እንደ ጤና አለመቆጠሩም መሰረታዊ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ።

ይህ ለወትሮውም ትኩረት የተነፈገው የአይምሮ ጤና ችግር በኮቪድ 19 ምክንያት እጅግ እየተባባሰ መሄዱ እውን ነው። ከኮቪድ በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ የሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ግጭት እና ጦርነት ያስከተሉት ግድያ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመትም ለአይምሮ መታወክ ተጨማሪ ምክንያት መሆናቸውን ዶክተር ሙሉቀን ነግረውናል። ታዲያ ሀገሪቱን ከዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማላቀቅና ለሀገር ሰላምም ሆነ ልማት ለማምጣት የአይምሮ ጤና ከአካላዊ ጤና እኩል አስፈላጊ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ ባለሙያዎቹ የመክራሉ።

XS
SM
MD
LG